ኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርትን ለማሳደግ የሰራውን ውጤታማ ሥራ በእንስሳት ሃብት ልማትም ለማከናወን እንዲዘጋጅ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርትን ለማሳደግ የሰራውን ውጤታማ ሥራ በእንስሳት ሃብት ልማትም ለማከናወን እንዲዘጋጅ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የሰብል ምርትን ለማሳደግ የሰራውን ውጤታማ ተግባራት በእንስሳት ሃብት ልማትም ለማከናወን እንዲዘጋጅ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በሚል ስያሜ ሲጠራ የቆየው ተቋም ተልዕኮውን በማሳደግ ወደ ኢንስቲትዩት በማደግ በዛሬው እለት በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን፤ ተቋሙ በተለይም የሰብል ምርትን ለማሳደግ የሰራውን ውጤታማ ሥራ አድንቀዋል።
አሁን ላይ ከኤጀንሲ ወደ ኢንስቲትዩት መሸጋገሩ ደግሞ ተልዕኮውን ከፍ በማድረግ የሰብል ምርትን ለማሳደግ የሰራውን ውጤታማ ተግባራት በእንስሳት ሃብት ልማት ለማከናወን ያስችለዋል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በግብርና መረጃ ትንተና ላይ አመርቂ ተግባር እያከናወነ መሆኑን በማንሳት በአሰራር ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ ለግብርና ሚኒስቴር አቅም እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በሚኒስትሩ ሥር ከሚገኙ ዘጠኝ ተቋማት መካከል ኢንስቲትዩቱ አንዱ በመሆኑ በጥናትና ምርምር ምርታማነትን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፤ ተቋሙ ተልዕኮውን በማሳደግ ወደ ኢንስቲትዩት ማደጉን በስኬት አንስተዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመለየትና በማጥናት የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ ወደ ዘመናዊ አሰራር ለማሳደግ የሚደረገውን የምርምር ሥራ ለማሻሻል እና የፈጻሚ አካላትን አቅም ለመገንባት እየሰሩ መሆኑንም አስታውሰዋል።
ኢንስቲትዩቱ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን የዘመናዊ ግብርና ዘዴ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በሲዳማና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች በስፋት እየሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በቀጣይም ተደራሽነቱን ወደ ተቀሩት የሀገሪቱ ክልሎች ለማስፋት መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡