ቀጥታ፡

የጠላትን አላማ ማክሸፍ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ተደርጓል- ሌተናል ጀኔራል ናስር አባዲጋ

መተማ፤ ሰኔ 23/2014 (ኢዜአ)፡ ''የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን ማደናቀፍ እንደማይቻል ጠላቶችና ተላላኪዎች መገንዘብ አለባቸው'' ሲሉ በመከላከያ ሠራዊት የ8ኛ ማዕበል ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ናስር አባዲጋ ተናገሩ።

 የ8ኛ ሜካናይዝድ 2ኛ ብርጌድ ጀብድ ለፈፀሙ የሠራዊት አባላትና አመራሮች በገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር በተካሄደው መርሐ ግብር እውቅናና ሽልማት ሰጥቷል።

የሜካናይዝድ ክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ናስር አባዲጋ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ረፍት የነሳቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች የትንኮሳ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው።

በየትኛውም አቅጣጫ ትንኮሳ ለሚሞክር አካል የጠላትን አላማ አስቀድሞ ለማክሸፍ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሩ የአሸባሪውን ህወሓት ጥቃት በመመከት ያሳየውን ጀግንነት ዛሬም በላቀ ብቃትና ወኔ የትኛውንም ጠላት ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  እንዳይደናቀፍ ሠራዊቱ ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል።

"የሀገርን ህልውና ለማስቀጠል መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችን ታሪክ ሲያወሳቸው ይኖራል" ብለዋል።

እውቅናና ሽልማቱ  ለሀገርና ህዝብ እንዲሁም ለሠራዊቱ ክብር ሲሉ በታማኝነት የተፋለሙ የሠራዊት አባላትን እውቅና የሰጠ መሆኑን አመልክተው፤  ይህም ለቀጣይ ለላቀ የግዳጅ ጀብድ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ያለባት ችግር ካለፈው ቢያንስ እንጅ የሚብስ አይደለም" ያሉት ደግሞ የብርጌዱ ዋና አዛዥና የ8ኛ ሜካናይዝድ ምክትል አዛዥ ኮሌኔል ዳኛቸው በቀለ ናቸው።

የብርጌዱ አመራርና አባላት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የተሰጣቸው ሽልማትና እውቅና ለላቀ ግዳጅና ጀብድ ዝግጁ የሚያደርጋቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ 1ኛ ደረጃ ሜዳይ ተሸላሚ የሆኑት ሻምበል ኩማ ሃደረው ናቸው።

"ሞት ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ የህይወት አንድ ገፅታ ነው" ያሉት ሻምበል ኩማ፤ ታሪክ በመስራት ከመሬት በላይ የሚውል ስም ይዞ ለማለፍ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በእውቅና እና ሽልማት  መርሐግብሩ የምዕራብ ጎንደር ዞንና የገንዳ ውሃ ከተማ አስተዳደር የምስጋና እውቅና ተስጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም