ወጣቱ ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃይሎችን ሊታገል ይገባል - ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

65

ሀረር፤ ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ወጣቱ የህዝቡን የአብሮነት እሴት በመሸርሸር ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃይሎችን ሊታገል ይገባል ሲሉ የሃረሪ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ፡፡

የሃረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ‘’በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ’’ በሚል መሪ ሀሳብ ዘንድሮ የሚካሄደውን  የወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ እና ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ ግብር አስጀምረዋል ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ  በመርሃግብሩ ማስጀመሪያ ላይ  እንዳሉት ወጣት በጎ ፈቃደኞች የሃገር ልማት እንዲጎለብት እና  የማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግርን ለመፍታት  የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው ፡፡

ወጣት በጎ ፈቃደኞች  ባለፉት አመታት  ባከናወኗቸው ተግባራት በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ አስተዋጾ ማድረጋቸውን  ገልፀዋል፡፡

በተለይም በሰላም እሴት ግንባት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በፅዳትና ውበት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣  በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎቸ ባከናወኗቸው ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አመልክተዋል ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ "በዘንድሮው የወጣች  የበጎ ፈቃድ መርሃግብርም በሰላምና ደህንነት ብሎም  የመቻቻል ባህልን የማያጎለብቱ ስራዎች ይሰራሉ" ብለዋል ፡፡

ወጣቱ በተለይም የማህበረሰቡን የአብሮነት እሴትን በመሸርሸር ሃገር ለማፍረስ የሚታትሩ ሃይሎችን  ሊታገላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ወጣቱ በክረምት በጎፈቃድ መርሃግብር  በስፋት እንዲሳተፍ ርእሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

በባለፈው አመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት  ከ21 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ከ 38 ሚሊየን በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን   ያስታወሱት ደግሞ  የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ናቸው፡፡

በመር ሃግብሩ የተሰጠው አገልግሎት በብር ሲተመን ከ 10 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያለው መሆኑንም አውስተዋል።

ሚኒስትሯ በዘንድሮው የበጎፈቃድ መርሃግብር ከ19 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ  በአርንጓዴ አሻራ፣ የግብርና ልማት፣ የሰላም እና ደህንነት  በመሳሰሉ በርካታ ተግባራት የሚከናኑ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በህልውና ዘመቻው ሀገር የልጆቿን ድጋፍ በፈለገችበት ጊዜ ወጣቱ በግንባር በመዝመት ለሃገር ክብር ህይወቱን የሰጠ የሃገር ባለውለታ መሆኑን ሚኒስትሯ  አስታውሰዋል ፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃግብር  ወጣቶች ለሀገራቸው ዋልታና መከታ መሆናቸውን ከሚያረጋግጡበት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

"መርሀ ግብሩ ወጣቶች ከማህበረሰቡ የተለያዩ ባህልና ወጎችን እንዲቀስሙ ትልቅ አስተዋፆ አለው "ብለዋል ፡፡

ርእሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ከየሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጋር በበጎ ፈቃድ ስራ ለእናት ሃገር ከፍታ ለመስራት የተዘጋጀ ሰነድ ተፈራርመዋል ፡፡

 ርእሰ መስተዳድሩ  ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም ከፍተኛ የፌዴራል እና ክልል መንግስት የስራ ሃላፊዎች እና  የበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እንዲሁም ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር በጋራ በመሆን ችግኝ በመትከል  የአረንጓዴ አሻራ ያሳረፉ ሲሆን የአቅመ ደካማ ህብረተሰብ ክፍሎችን የቤት እድሳት አስጀምረዋል ፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብርሩ ‘’በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ’’ በሚል መሪ ቃል ለሁለት ወር እንደሚካሄድ ተመላክቷል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም