ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት አላት- የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

111

ሰኔ 22 ቀን 2014(ኢዜአ) ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡርኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በትናንትናው ዕለት ከኩባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የኩባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቡርኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ትብብራቸውን ወደ ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው ኩባ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ዘርፍ ግኑኝነት ለማጠናከር ያሳየቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለሚገኘው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ዙሪያ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እ.አ.አ ከ1975 ጀምሮ የተመሠረተው የኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም