ቀጥታ፡

የግብርና አሰራሩን ከመሰረቱ በመለወጥ በምግብ እህል ራስን ለመቻል በሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው--የግብርና ምርምር ማእከላት

አዳማ ሰኔ 22/2014 (ኢዜአ) በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የግብርና አሰራሩን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የግብርና ምርምር ማእከላት ገለጹ ።

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ቦጋለ ለኢዜአ እንደገለጹት  በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የግብርና አሰራርን ማዘመንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ አስፈላጊ ነው።

የክልሉ ግብርና ምርምር በስሩ በሚገኙ 17 ማዕከላት አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማውጣትና በማላመድ አርሶ አደሩ እንዲጠቀማቸው በማጋዝ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየተሰራ ነው ብለዋል።

ግብርናውን ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማመንጨት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት ከተውጣቱ  ሙሁራንና ተመራማሪዎች ጋራ እየተሰረ መሆኑን ተናግረዋል።

ግብርናውን ከመሰረቱ ለመለወጥ ከአራት ዓመት በፊት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የፌዴራል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፎቶ ኢስሞ ናቸው።

በተለይ በቴክኖሎጂ፣በጥናትና ምርምር፣በፖሊስ ማማከር፣በገጠር ፋይናንስና በሌሎች መስኮች ዘጠኝ የግብርና ሴክተር ማነቆዎች በጥናት ተለይተው መቅረባቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ አበራ ወርቁ እንደገለጹት የክልሉን ግብርና ለመለወጥ ከተቀረፁት  ተግባራት መካከል 17ቱ እየተተገበሩ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮ ዓመት ብቻ 6ቱ ወደ ተግባር ገብተዋል ነው ያሉት።

የበጋ ስንዴ፣የቢራ ገብስ፣ የአቮካዶና የሙዝ ልማት፣የማር፣ቡናና ሻይ ልማትን ተግባራት እንደሚገኙበትም ለአብነት ጠቅሰዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱረህማን አብደላ በበኩላቸው የግብርና አሰራሩ ኋላቀር መሆን በምግብ ራሳን ለመቻል በሚደረገውን ጥረት ላይ ማነቆ ሆኗል።

የግብርናውን ዘርፍ በእውቀት፣በቴክኖሎጂና በሳይንስ የመደገፍ ሂደት ዝቅተኛ መሆኑን ዋነኛ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር ማዕከላት የሚፈለቁ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ጋር የሚይደርሱበት ሂደት ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የግብርና ሽግግር ምክር ቤት በአሰራሮች፣የህግ ማእቀፎችን በአዋጅ በማስደገፍ መቋቋሙን ገልጸው ምክርቤቱ ከምርምር ማዕከላት ጀምሮ እስከ አርሶ አደሩ ድረስ ተመጋጋቢና የተቀናጀ ስራ ለመስረት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

አዲሱ አሰራር የግብርና ሽግግሩን ማሳካት እንደሚያስችል የገለጹት አቶ አብዱረህማን ክልሉን በሰባት ስነ ምህዳር በማደራጀት ወደ ተጨባጭ ስራ እየተገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

የተፈጠረው አደረጃጀት በአየር ጸባይና በስፋት በሚመርቱ ሰብሎችን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቁመው የስንዴና ቢራ ገብስ፣የጤፍና ቆላ ጥራጥሬ፣የቦቆሎ፣የአቮካዶና ሙዝ፣የቡናና ሻይ፣የጫትና የእንስሳት ሀብት ልማት  ክላስተሮቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አደረጃጀቱ እውቅትን፣ጉልበትንና ሀብትን በአንድ ላይ በማቀናጀት የግብርና ሽግግሩን ግብ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም