የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ገቡ
ሰኔ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑክ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ ባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ገብቷል፡፡
ልዑኩ ጎባ-ሮቤ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ፣የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሀደ ሲንቄዎች ተገኝተው ተቀብሏቸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዞኑ በመንግስት በጀትና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የበጀት ድጋፍ የግንባታ ሥራቸው የተጠናቀቁ የልማት ፕሮጀክቶችን በይፋ መርቀው ስራ ያስጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከሚመረቁት የመሰረተ ልማቶች መካከል በሮቤ ከተማ አስተዳደር የተገነቡ አራት ትምህርት ቤቶች፣የእናቶችና ህጻናት የህክምና ማዕከል፣ የባሌ ዞን አስተዳደር ህንጻ እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
እንዲሁም በባሌ ኦሮሞ የጸረ-ጭቆና ትግል ውስጥ ትልቅ ቦታ ለነበራቸው ጀነራል ዋቆ ጉቱ መታሰቢያነት የተገነባ ሃውልትንም ያስመርቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከሰኔ 20/2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣባቸው ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ የክልሉ መንግስት ቀደም ብሎ መግለጹ ይታወሳል፡፡