በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ ግጭቶችን ስርዓት ዘርግቶ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ ሰነድ ተዘጋጀ

34

ሰኔ 21/2014 /ኢዜአ/ በተለያዩ ምክንያቶች በአገሪቷ የሚከሰቱ ግጭቶችን ስርዓት ዘርግቶ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ስትራቴጂ ሰነድ ማዘጋጀቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ''የብሔራዊ ግጭት መከላከልና ሠላም ግንባታ ስትራቴጂ'' በሚል በተዘጋጀ  ሰነድ ላይ  ከፌደራልና ክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።   

በውይይቱ ላይ የክልል እና የፈዴራል ተወካዮች፣ አፈ ጉባኤዎች እና የጸጥታ ዘርፍ ኃፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በሰነዱ ላይ ሊካተቱ የሚገቡ ጉዳዮችም ተዳሰዋል።   

ሰነዱን እውን ለማድረግ ግጭቶች እንዴት ቀድሞ መከላከል ይቻላል? ሲከሰቱስ እንዴት መፍታት ይቻላል? ለሚለው በጥናት የተደገፈ ምላሽ የያዘ መሆኑም ተመላክቷል።     

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  አገኘሁ ተሻገር፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።  

ግጭትን ስርዓት ዘርግቶ በዘላቂነት ለመፍታት ደግሞ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂ መቀየስ ማስፈለጉን አስረድተዋል።        

በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጀው ብሔራዊ ግጭት መከላከልና ሠላም ግንባታ ስትራቴጂ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።   

የብሔራዊ ግጭት መከላከልና ሠላም ግንባታ ስትራቴጂ ወደ ሥራ ሲገባ ግጭት ሳይፈጠር ቀድሞ ለመከላከልና ችገሮችን ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የሰነዱን ይዘት በማብራራት ለውይይት ያቀረቡት አቶ ብዙነህ አሰፋ፤ ከዚህ በፊት ግጭቶች ሲከሰቱ ጊዚያዊ መፍትሄ መስጠት ብቻ የነበረ መሆኑን አስታውስው የተዘጋጀው ስትራቴጂ የግጭት መንስኤዎች ላይ በማተኮር ቀድሞ መከላከል ያስችላል ብለዋል።

የግጭቶቹን መንስኤዎች ለይቶ መፍትሄ የሚያመላክት ሰነድ መሆኑን አብራርተው በሰለጠነና ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ የሚያደርግ በመሆኑን ጠቁመዋል።     

የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንዓ ያደታ፤ የስትራቴጂውን መዘጋጀት በማድነቅ ለሰላም ግንባታ ሂደት ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት ብለዋል።  

በርካታ የአፍሪካ አገራት ሠላም ላይ ትኩረት ያደረገ ስርዓተ- ትምህርት ያላቸው መሆኑን አስታውሰው በኢትዮጵያም ይህ ተሞክሮ ሊሰፋ ይገባል ነው ያሉት።   

 በፌደሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና ሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ከበደ፤ አገር በቀል ግጭት አፈታት እውቀቶችን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።  

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንታዬ ተስፋዬ በበኩላቸው ለግጭቶች መንስኤ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የእሴቶች መሸርሸር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ስትራቴጂው እሴቶች ላይ የሚያተኩር መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም