የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል-ወጣቶች

73

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዜጎችን ሰላምና ደህንነት፣ ፍትሃዊ የአገልገሎት አሰጣጥና የወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የአዲስ አበባ ወጣቶች ጠየቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት በመዲናዋ ከሚኖሩ ወጣቶች ጋር በሰላም፣ደህንነትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አካሂዷል።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ብልፅግና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሠ ዓለሙ፣ የፓርቲው አመራሮችና የከተማዋ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

ወጣቶች በመዲናዋ ሰው ተኮር የሆኑና የነዋሪዎቿን ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ለመቀየር የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያቃለሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በወጣቱም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱና በቅድሚያ ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች እንዳሉ በመጠቆም።

በዋናነትም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችና ግድያዎችን በማስቆም አስትማማኝና ዘላቂ የሰላምና ደህንነት ማስከበር ስራዎች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

በከተማዋ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ጥረት ቢደረግም ችግሩ ባለመፈታቱ አሁንም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የማህበረሰቡ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗልም ብለዋል።

በፍትሃዊ የስራ እድል ተጠቃሚነት ዙሪያ ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ የጀመራቸውቅ ተግባራ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት አክሊሉ ታደሰ የከተማዋ ወጣቶች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለሰላም፣ለልማትና ለብልጽግና ጉዞ መሳካት እየተጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዘመናዊ የፖለቲካ ባህል አንድነትን በማጠናከር ልዩነቶችን ማክበር፣ ሀገር የጋራ መሆኗን በማመን ለእድገቷ እጅ ለእጅ መያያዝና ለሰላም ቁርጠኛ ሆኖ አስተዋጽኦ ማበርከት አስፈላጊ መሆናቸውን አንስቷል።

በዚህም ወጣቶች በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ ቁርሾን ከሚፈጥሩ አመለካከቶች በመራቅና ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ወጣት አክሊሉ ጠቁሟል።

በመሆኑም ለሰላም እጦት መንሰኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና በመታገል በሃላፊነት ሀገርን ማሻገር ከወጣቱ እንደሚጠበቅም አክሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ መለሰ አለሙ በበኩላቸው ከወጣቶቹ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን በማመን ችግሩን ለመቅረፍ የወጣቱን ሚና ማጉላት ያስፈልጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ጥያቄ እንዳይሆን ከተማ አስተዳደሩ ከጸጥታ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የከተማዋን ነዋሪዎች በተለይም በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ ሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ወጣቶች የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታን መረዳትና ማጤን እንደሚጠበቅባቸው፣ በተለይም ኢትዮጵያ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳትላቀቅ የሚሰሩ አካላት አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

ውይይቱ "የእኛ ዘመን ወጣት ሚና" በሚል መሪ ቃል ነው የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም