የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት የማስከበር ሁለንተናዊ ብቃትና ቁመና አለው

60

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት የማስከበር ሁለንተናዊ ቁመና ያለው መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገለጸ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የምርኮኞችን አያያዝ ባልጠበቀ መንገድ ወታደሮቼን ገድሏል በሚል የሱዳን ጦር የሚነዛው መረጃ መሰረተ ቢስ መሆኑንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቦታው እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ የገባው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር ግጭት መፍጠሩ ታውቋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ፤ አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋና ጥቃት በፈጸመበት ወቅት የሱዳን ሰራዊት የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝብ ታሪካዊ ወዳጅነትን በማይመጥን መልኩ በኢትዮጵያ ግዛት ላይ የክህደት ወረራ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ በመሆኑ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ እርምጃ ከመግባት ተቆጥቦ መቆየቱንም ገልጸዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል የአገሩን ፖለቲካዊ ትኩሳት እና ሕዝባዊ ጫና ለማርገብ ሲል ወቅት እየጠበቀ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እና ዛቻ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ለዚህ የሱዳን ጦር ትንኮሳ የኢትዮጵያ ሠራዊት በኃይል ምላሽ አለመስጠቱንና ሁኔታዎችን በትዕግስት ማሳለፉን አስታውሰዋል።

ከሰሞኑም የሱዳንን ወታደራዊ ኃይል ከከዱና ከአሸባሪው ሕወሓት አባላት ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቆ በመግባት በአካባቢው ሚሊሻዎችና ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና ከሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ የሱዳን ወታደራዊ ኃይል እውነታውን ገልብጦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሥፍራው ባልነበረበት ሁኔታ ቀድሞ ከሳሽ ሆኖ ቀርቧል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሠራዊት ምርኮኞችን መቀጣጫ አድርጎ ክብር ያልጠበቀ አያያዝ መያዙን፣ ሲቪል መግደሉን በመጥቅስ፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ዛቻ የተሞላበት መግለጫ ማውጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቦታው አልነበረም ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ ምርኮኞችን ቢይዝ እንኳን ሕግ አክባሪነት፣ ሕዝባዊነትና ግዳጅ አፈጻጸም ብቃቱ በዓለም ሰላም ማስከበር ዘመቻ ጭምር ተመራጭ ያደረጉት የሠራዊቱ መለያ ባህሪያት ናቸው ብለዋል።

ሠራዊቱ ዲሲፕሊን ያለው፣ የኢትዮጵያዊነትን ሞራል ልዕልና የጠበቀ፣ በሥርዓት ለውጥ የማይቀያየር የምርኮኛ አያያዝ የሚያውቅ ፕሮፌሽናል ሠራዊት እንደሆነም አስረድተዋል።

ከጥንት ጀምሮ በኮሪያና በኮንጎ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ጭምር የተመሰከረለት መሆኑን አስታውሰው በአብዬ ግዛት የሰላም ማስከበር ተልዕኮም በብቸኝነት የተመረጠ ሠራዊት እንደሆነ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የአካባቢው ሕዝብና ሚሊሻም የዚህ ጨዋነት እሴት ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲህ አይነት ባህሪያት እንዳለው እየታወቀ በሱዳን ወታደራዊ ኃይል በኩል ከእውነታው የራቀ መግለጫ መስጠቱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

"ምናልባትም የሱዳን ወታደራዊ ኃይል የተሳሳተው ያስጠጋቸው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አባላት ከሆኑ ወደ ፊትም ለተመሳሳይ ስህተት እንዳይዳርጓቸው እንመክራለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ ከመንግሥት ትዕዛዝ ከተሰጠው እርምጃ ለመውሰድ በቂ ምክንያት እንዳለው አብራርተዋል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው እንደ ሽፍታ ቡድን ሳይሆን እንደ መደበኛና ዘመናዊ ጦር በግልጽ በታወጀና በታወቀ መልኩ በኃይል ከተያዘ ግዛት በማስወጣት የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ሁለንተናዊ ቁመና እንዳለው አረጋግጠዋል።

የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ለዘላቂ ሰላም ሲባል ማጣራት ከተፈለገ ከሁለቱ አገራት መከላከያ ሠራዊት የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲጣራ ለመተባበር የኢትዮጵያ ሠራዊት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም