ከጸጥታ አካል ጋር በመቀናጀት የአሸባሪውን ሸኔና የሌሎች ፀረ ሰላም ቡድኖችን ሴራ ለማምከን እንሰራለን - የዞኑ ወጣቶች

ግምቢ፡ ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከጸጥታ አካል ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የአሸባሪውን ሸኔና የግብረአበሮቹን እኩይ ሴራ ለማምከን እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የምዕራብ ወለጋ ዞን ወጣቶች ተናገሩ፡፡

“ምክንያታዊ ወጣቶች” በሚል መሪ ሀሳብ የወጣቶች ምክክር መድረክ ዛሬ በጊምቢ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በዞን ደረጃ በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉ ወጣቶች በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የጠላት ሴራ ለመመከት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።ሁሉም ወጣት የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ባሻገር ከመንግስት የጸጥታ አካል ጋር በመሰለፍ የአሸባሪውን ሸኔና የሌሎች ፀረ ሰላም ቡድኖችን የጥፋት ድርጊት መመከት የነገ ሀገር ተረካቢ ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

በመድረኩ የተሳተፈው ወጣት ገመቺስ መኮንን በሰጠው አስተያየት ወጥቶ መግባትና ሰርቶ መለወጥ የሚቻለው የዜጎች ሰላም ሲረጋገጥ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም አለበት ብሏል።

በተለይ የሀገር ሰላምና እድገትን አጠናክሮ በማስቀጠል ሂደት እንደ ወጣት ያለበትን ድርሻ ለመወጣት እንደሚሰራ ተናግሯል።

"አሁን ላይ በአካባቢያችን እየተስተዋለ ያለውን የጠላት እኩይ ተግባርና ሴራ ለማምከን የዞኑ ወጣቶች በአንድነት እንቆማለን "ሲል ተናግሯል።

"ሰላምና እድገት በሀገሪቱ እንዲረጋገጥ ለውጡን የመጠበቅ ሃላፊነት የወጣቱ ቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ተቀናጅተን እንሰራለን" ያለው ደግሞ ወጣት ሲሳይ ተስፋ ነው።

"በአሁኑ ወቅት በወጣቱ መስዋእትነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከሀገር ውስጥ ጋላቢዎቹና ከውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋት ሴራን እየፈጸመ ያለውን ሸኔና ግብረአበሮቹን ለማምከን በሚሰራው ስራ ላይ ድርሻችንን እናጠናክራለን" ሲል አመልክቷል፡፡

"ወጣቱ በየትኛውም የጠላት ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል በትግሉ የመጣውን ለውጥ ማስቀጠልና የሚፈለገውን ግብ እንዲያሳካ መስራት ይጠበቅበታል" ነው ያለው።

በምዕራብ ወለጋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሊላ ተረፈ እንደገለፁት "ለውጡ ያልተዋጠላቸው የኢትዮጵያን መፍረስ የሚፈልጉ ቡድኖች ያላደረጉት ሙከራ የለም።

"የለውጡ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ሃይል አንድነቱን በማጠናከር ዛሬም የሀገር አፍራሾችን ሴራ በማክሸፍ ሰላምንና ልማትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የወጣቱን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ሰሞኑን በዞኑ በቶሌ ቀበሌ በአሸባሪው የሸኔ ቡድን የተፈፀመውን የንጹሃን ግድያ እንደሚያወግዙ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም