ባለስልጣኑ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ለግብር መክፈያ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በወቅቱ እንዲጠቀም አስገነዘበ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ለግብር መክፈያ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በወቅቱ እንዲጠቀም አስገነዘበ
ሐዋሳ ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ለግብር መክፈያ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ በወቅቱ እንዲጠቀም የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን አስገነዘበ።
የ2014 ግብር ዘመን የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ጉድራ በመድረኩ ላይ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሚገኘው ግብር ከፋይ በወቅቱ ግዴታውን የማይወጣ ከሆነ በራሱና በታክስ ማእከላት ላይ ጫና ያሳድራል።
በተለይ ለእንግልትና ለግብር አከፋፈል ሥርዓት መዛባት መንስዔ እንደሚሆን አመላክተዋል።
አብዛኛው ግብር ከፋይ በመዘናጋት መጨረሻ ቀናት ላይ ከመጨናነቅና ወደ ቅጣት ከመግባት ለመዳን ጊዜውን በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በክልሉ ከሚገኙ 45 ሺህ ግብር ከፋዮች መካከል 35 ሺህ 241ዱ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ መሆናቸውን ጠቅሰው ከደረጃው ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 እስከ 30 ቀን 2014 ዓም ድረስ 180 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን አመልክተዋል።
የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የመክፈያ ጊዜ ከሐምሌ 1 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓም እንዲሁም የደረጃ ሀሌታ “ሀ” ደግሞ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓም መሆኑን አስታውቀዋል።
ሁሉም ግብር ከፋዮች ቀኑ ከመድረሱ እና ከመጠናቀቁ በፊት በመርሃ ግበሩ መሰረት ግብራቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።
የንቅናቄ መድረኩ ግብር ከፋዮች ከተሰጣቸው ጊዜ ገደብ ውጪ የሚከፍሉ ከሆነ አላስፈላጊ ወለድና የቅጣት ጫና ሊደርስባቸው እንደሚችል ለማስገንዘብ ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 98 ነጥብ 2 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።
በሚቀጥለው በጀት ዓመትም 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ከክልሉ ለመሰብሰብ ማቀዱን አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲዳማ ክልል ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ዘሪሁን ቃቢሶ በሰጡት አስተያየት ግብር ከእኛው ለእኛው የሚሰበሰብ ገቢ በመሆኑ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ ግብርን በወቅቱ እና በታማኝነት በመክፈል ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል።
በተለይ ከግብርታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለመንገድ እና ለሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች የሚውል መሆኑን በመረዳት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግዴታውን በመወጣት የልማት አጋርነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"በአንፃሩ ታክስን መሰወር በሀገር ላይ የሚደረግ ታላቅ ክህደት በመሆኑ ህብረተሰቡ ለፈፀመው ማናቸውም ግዢ እና አገልግሎት ደረሰኝ መጠየቅን ባህሉ ሊያደርግ ያስፈልጋል " ብለዋል።
በተለይ ግብርን የሚሰውሩ እና የሚያጭበረብሩ አካላትን በማጋለጥ ተገቢውን ትብብር ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሲዳማ ክልል የብላቴ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቶማስ አናቶ በበኩላቸው ግብር መንግስት የመሰረተ ልማት እና የአገልግሎት ወጪ የሚሸፍንበት የፋይናንስ ምንጭ የሚገኝበት ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዓላማውም እድገትን የማፋጠን፣ የዋጋ ግሽበት እንዳይኖር፣በዜጎች መካከል ፍትሃዊ የሀብት ስርጭት እንዲኖር የማድረግና የተመጣጠነ አካባቢያዊ ዕድገትን ማረጋገጥ ማስቻል በመሆኑ ሁሉም ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበጀት ዓመቱ ከወረዳው ለመሰብሰብ የታቀደውን 28 ሚሊዮን ብር ገቢ ሙሉ ለሙሉ በማሳካት ወረዳው ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠር እንዲሁም የታቀደውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
በንቅናቄ መድረኩ ላይ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከማአከል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።