የተሻሻለው የስፖርት ማህበራት አደረጃጀትና አሰራር መመሪያ የስፖርቱን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሻሻል ያግዛል-የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

64

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተሻሻለው ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት አደረጃጀትና አሰራር መመሪያ የስፖርቱን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሻሻል እንደሚያግዝ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ፡፡

መመሪያው የስፖርት አሶሴሽኖችና ፌዴሬሽኖች እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያደራጁ እድል እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት አደረጃጀትና አሰራር መመሪያ በቅርቡ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ መመሪያውን በሚመለከት በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሃሳቦችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

መመሪያው በስፖርት ዘርፉ ውስጥ ያሉ ፌዴሬሽኖችንና አሶሴሽኖችን እንደሚያዳክም የሚያነሱም አሉ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስት የስፖርት ማህበራትን ለማደራጀት ገንዘብን ጨምሮ የቴክኒክና ስልጠና ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡መንግስት ለስፖርቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ደግሞ የህግ ማዕቀፎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስፖርት ማህበራት አደረጃጀት በተመለከተ ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖራቸውና ብቁ ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

የፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች መጠናከር በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ስፖርተኞች ማፍራት ያስችላል።

ከዚህ አኳያ አንዳንዶች መመሪያው ማህበራቱን የሚያጥፍና ሰራተኛ የሚበትን ነው በሚል የሚያቀርቡት ሃሳብ የተሳሳተ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን የሚሉት መመሪያውን በትክክል ካለመገንዘብ የመነጨና ሆን ተብሎ ውዥብር ለመፍጠር ያለመ ሃሳብ መሆኑን ጠቁመዋል።

መመሪያው የስፖርት አሶሴሽኖችና ፌዴሬሽኖች እስከ አራት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን እንዲያደራጁ እድል እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የአቅም ውስንነት ያለባቸው ፌዴሬሽኖችና አሶሴሽኖች ራሳቸውን እንዲያበቁ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።

የተሰጣቸውን ጊዜና ድጋፍ በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ተያይዞ መስፈርቱን የማያሟሉ ማህበራት መታጠፋቸው እንደማይቀርም ነው ያነሱት፡፡

ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ መሰረት የማህበራት ምዝገባ እንደገና የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም