ቀጥታ፡

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት መቼም አይሳካለትም - ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት መቼም አይሳካለትም ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የክልሉን የ2014 ዓ/ም በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሁኔታን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም በክልሉ ከፍተኛ ስራ አፈጻጸም ቢኖርም እንደ አገር እና እንደ ክልል የገጠሙ 5 ትልልቅ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡እነዚህም ጦርነት፣ ድርቅ፣ ኮቪድ፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እንዲሁም የሸኔ የሽብር ቡድን ያደረሳቸው ጥፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው የሸኔ ቡድን ዜጎችን በጅምላ መግደል፣ መዝረፍና ማሰቃየትን ጨምሮ አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲፈጽም መቆቱን ገልጸዋል፡፡

ሸኔ የራሱ የሆነ ሃሳብ የሌለው፣ ለሌሎች ሃይሎች ተላላኪ የሆነና እኩይ ሃሳቡን በጉልበት ህዝብ ላይ ለመጫን የሚፈልግ ቡድን መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ለኦሮሞ ህዝብ የሚያስረዳው አጀንዳ የሌለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አረመኔነቱን ያስመሰከረበትን ተግባር በህዝብ ላይ እየፈጸመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህ አሸባሪ ቡድን ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ዙሪያ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡

ቡድኑ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት ወንድማማች የሆኑ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦችን ለማጋጨት በማሰብ ቢሆንም ይህ መቼም አይሳካለትም ብለዋል፡፡

የሁለቱን ክልል ህዝቦች በማጋጨትም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓላማ አድርጎ ቢንቀሳቀስም የህዝቹን አንድነት እና አብሮ የመኖር እሴት ግን ማንም ሊያጠፋው እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ላይ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ አካላት ጠንካራ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሣራ እየደረሰ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም ቡድኑን ለማጥፋትና ህዝቡ ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጥቃት ለማስቆም ከህዝቡ ጋር በመሆን የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ፣ የህዝቡ ተጠቃሚነት ተረጋግጦ እንዲቀጥል የተጀመረው አሸባሪው ሸኔን የማጥፋት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም