ቀጥታ፡

ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች በመደምሰስ የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንሰራለን - የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች በመደምሰስ የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ እንሰራለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ያካሄዱት ስብሰባ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ኮሚቴዎቹ በሰላምና ደህንነት፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊ፣ በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት መደረጉን ተናግረው፤ በቅርቡ በጋምቤላና በምዕራብ ወለጋ የተፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት መወገዙን ተናግረዋል።

የተጀመረው የህግ ማስከበር ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው፤ በተወሰደው እርምጃም በርካታ የሽብር ቡድን አባላት መደምሰሳቸውን ተናግረዋል።

የጠላት ሚዲያዎች የተዛባ መረጃ በማስተጋባት ውዥንብር እየፈጠሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በንፁሃን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ መንግሥትና ህዝብ በልማት ላይ ያላቸውን ትኩረት ለማዛባት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌትና የሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ጅማሮን ለማደናቀፍ ነው ብለዋል።

አርሶአደሩ የመኸር እርሻ ሥራ ላይ ተረጋግቶ እንዳይሠራ የታቀደ እኩይ ድርጊት መሆኑን ገልጸው፤ የሽብር ቡድኖቹ ድርጊት የትኛውንም ብሔር አይወክልም ነው ያሉት።መንግሥትና ህዝብ በጋራ በመቀናጀት የጠላትን ሀገር የማፍረስ እኩይ አላማ ይቀለብሱታል ብለዋል።

በኮሚቴዎቹ ስብሰባ የውስጠ ፓርቲ ጉዳዮች መገምገማቸውን ገልጸው፤ ብልጽግና ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱ የተጠናከረ ፓርቲ መሆኑን ታይቷል ነው ያሉት ውስጠ ፓርቲ ዲሲፕሊንም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዉ ስኬቶችና ጉድለቶች መገምገማቸውን ገልጸው፤ ማክሮ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን መዛባት ለማረጋጋት ሀገር በቀል ሪፎርም በማድረግ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም