ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የኮንትሮባንድ እቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

172

ሰኔ 20 ቀን 2014(ኢዜአ)የጉምሩክ ኮሚሽን በአንድ ሳምንት ውስጥ 46 ነጥብ 6 ሚሊዮን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃ እና 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የወጭ ኮንትሮባንድ እቃ በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን ገልጿል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋለው የኮንትሮባንድ እቃ መካከል አልባሳት፣ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃው በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በብርበራና በጥቆማ የተያዘ ሲሆን ኮንትሮባንድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሶስት ሰዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪ ማቅረቡን ከኮሚኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም