ሸኔ በታሪክ ጠባሣ ሆኖ የሚቆይ ጥቃት በንጹሃን ላይ ቢፈጽምም በጸጥታ አካላት ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደበት ነው-አቶ ሽመልስ አብዲሳ

102

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)አሸባሪው ሸኔ በታሪክ ጠባሣ ሆኖ የሚቆይ ጥቃት በንጹሃን ላይ ቢፈጽምም በጸጥታ አካላት ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደበት መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን የ2014 የስራ ዘመን አጠቃላይ የስራ ሁኔታን እና የገጠሙ ፈተናዎችን በማስመልከት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በክልሉ የአፈጻጸም ሂደት ውስጥ 5 ትልልቅ ተግዳሮቶች መግጠማቸውን ገልጸዋል።

እነኚህም በሰሜኑ የተደረገው ጦርነት፣የተከሰተው ድርቅ፣ ኮቪድ እና አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ፣ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የገጠሙ ተግዳሮቶች እና የሸኔ የሽብር ቡድን ያደረሳቸው ጥፋቶች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

አሸባሪው የሸኔ ቡድን በህዝቡ መሃል እየተሽሎከሎከ በንጹሃን ላይ ጥቃት በመፈጸም ላይ መሆኑንም ጠቁመው የሽብር ቡድኑ የኦሮሞ ህዝብን በመግደል፣በመዝረፍ እና ሌሎች ህገወጥ ተግባራትን በማከናወን ጠላትነቱን በተግባር ማስመስከሩንም ገልጸዋል።

ሸኔ ተላላኪ፣የራሱ ሃሳብ የሌለው እና በጉልበት ብቻ ህዝቡን በማስፈራራት የሚያምን፣የኢትዮጵያ ጠላት ነው ሲሉ አመልክተዋል።

ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ ግምቢ ዙሪያ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት ሁለቱን ብሔሮች በማጋጨት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓልሞ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው ቡድኑን ለማጥፋት የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና የሽብር ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ኪሣራ እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ለረጅም ዘመናት አብረው የኖሩ፣ የተጋመዱ እና ማንም ሊለያቸው የማይችል መሆኑንም በመጠቆም አሸባሪው ሸኔ ፍርሃትን ኢትዮጵያ ላይ ለማንገስ እና በአገሪቱ የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ በማለም ቢንቀሳቀስም ዓላማው መቼም አይሳካም ብለዋል።

ሸኔ በታሪክ ጠባሣ ሆኖ የሚቆይ ጥቃት በንጹሃን ላይ ቢፈጽምም በጸጥታ አካላት የእጁን እያገኘ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም