ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የ2014 ዓም የወጣቶች የክረምት እና የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ አስጀመሩ

58

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የ2014 ዓም የወጣቶች የክረምት እና የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በይፋ አስጀመሩ።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር በሰብአዊነት የሚከናወን እንዲሁም ድንበር የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰብን ማገልገል የዜጎችን የእርስ በእርስ መስተጋብርን ያጠናክራል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞች በሚሰማሩበት የበጎ ፈቃድ ስራ አምባሳደር በመሆን የዜጎች እና ሀገሪቱ ሰላም የማስጠበቅ እና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በሃላፊነት እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል እንዲያጎለብቱ ለማስቻል የተለያዪ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት፣ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ተግባራት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በዘንድሮ ሀገር አቀፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 19 ሚሊየን ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን 40 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዪ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል ብለዋል።

አያይዘውም የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ በዚህም 11 ቢሊየን ብር የሚተመን አገልግሎት ይሰጣል ነው ያሉት።

በይፋ የተጀመረው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ " በሚል መሪ ቃል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም