"አሸባሪዎችን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት በጋራ አጠናክረን እንቀጥላለን" -የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች

82

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት የአሸባሪዎች ፍላጎት እና ጥፋት የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት አይሸረሽረውም ብለዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ የተጨፈጨፉት ንጹኀን ወገኖች በመጀመሪያ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ይህን ደግሞ በጋራ አውግዘናል ነው ያሉት።

ሸኔ የአማራ ብቻ ጠላት አለመሆኑንና የጋራ የኢትዮጵያውያን ጠላት እንደሆነም ገልጸዋል።

ሸኔን ከማጥፋት ውጭ አማራጭ እንደሌለ ተወያይተናል፤ አቅጣጫም አስቀምጠናል ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ።

አሸባሪው ሕወሃት ጦርነት እየጎሰመ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል ይህንንም መመከት የምንችለው በጋራ ነው ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከዚህ በፊት የሁለቱ ሕዝቦች አብሮነት እየተገመደ እንጅ እየላላ አልሄደም፤ አሸባሪው ህወሓት ሲነሳ አንድነታችን ጠንክሮ በአንድ ጉድጓድ እንደተቀበርን አሸባሪው ሸኔ ሲነሳም አንድነታችን የበለጠ እንዲጠናከር አድርጎታል ብለዋል።

ሸኔ ጊምቢ ላይ ጥቃት የፈፀመው ሦስት ዓላማዎችን ይዞ ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ አንደኛ የአማራና የኦሮሞ ሕዝብን ለመለያየት ሲሆን ይህ ትላንት ሕወሓትም አስቦ ያልተሳካለት ሸኔም ዛሬ የማይሳካለት በእኛ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የማይሆን ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ፍርሐትን በሀገሪቱ ማንገስ ሲኾን ሦስተኛው ደግሞ ማሸበር ነው ብለዋል። ይህ እንዳይሳካ በጋራ ርምጃ እየወሰድን ነው ብለዋል።

ሁለቱ ሕዝቦች ትላንትም ዛሬም በጋራ መቆም እንደሚቻል ያሳዩ በመሆኑ ሸኔን መዋጋት አይከብዳቸውም ነው ያሉት።

ዛሬ አንድነታችንን የምናሳየው ጽንፈኝነትን በመዋጋት ነው ብለዋል።

ለሕዝባችን ለዓላማችን ስንል ትላንት መስዋእትነት እንደከፈልነው ነገም መስዋእትነት ከፍለን ኢትዮጵያን የተሻለች ሀገር እናደርጋለን ነው ያሉት።

ሸኔን ሽፋንና መረማመጃ አድርገው በአመራሩ ላይ የሚዘምቱ አመራሩን ለመከፋፈል የሚጥሩ አይሳካላቸውም ብለዋል።

የሁለቱ ክልል የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች አቶ ግርማ የሽጥላ እና አቶ ፍቃዱ ተሰማ ትላንት ወያኔ እሳት እና ጭድ ናቸው ብሎ በአንድነታችን ቢሳለቅም በጋራ እንደጣልነው ሁሉ የመከፋፈል ዓላማ ያለውን ሸኔን በጋራ እናጠፋዋለን ማለታቸውን የአሚኮ ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም