ኢራን ወደ ሕዋ ሮኬት አስወነጨፈች

603

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢራን የ ብሔራዊ ሕዋ ምርምር አካል ነው የተባለለትን አዲስ ሮኬት ማስወንጨፏን አስታውቃለች።

ሙከራውን ተከትሎ አሜሪካ ድርጊቱን ወታደራዊ አላማ አለው ስትል መግለጿን የሀገሪቱን ሚዲያ ዋቢ አድርጎ አርቲ ዘግቧል።

የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ኢራን የሕዋ ምርምር ተልዕኮ ያለው 25 ነጥብ 5 ሜትር የሚረዝም ባለ ሶስት ደረጃ ሮኬት ወደ ህዋ አምጥቃለች ሲል ገልጿል።

ሮኬቱ የተወነጨፈው ኢማም ኮህሜን ከሚባለው የህዋ ምርምር ማዕከል ሲሆን ሙከራው ኢራን ከሌሎች ሀገራት ጋር በሚመጣጠን መልኩ በሕዋ ምርምር ያላትን አቅም ለማጎልበት እንደሆነ ተነግሯል።

ሮኬቱ ወደ ምድር የተለያዩ የሳተላይት መረጃዎችን የሚሰጥ መሆኑ የገለጸ ሲሆን የሮኬት ሙከራው ስለመሳካት አለመሳካቱ ግን ምንም ያለው ነገር የለም ተብሏል።

ኢራን የሮኬት ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ የምታካሂደውን ሰፊ ምርምርና ሙከራ አሜሪካና አጋሮቿ ዘርፉን ለማይፈቀድ ወታደራዊ አላማ እየተጠቀመች ነው ሲሉ እንደሚከሷት ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም