በወናጎ ወረዳ ከ85 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ የተደረሰበት ማደያ ታሸገ - ኢዜአ አማርኛ
በወናጎ ወረዳ ከ85 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ የተደረሰበት ማደያ ታሸገ

ዲላ፡ ሰኔ 19/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ወናጎ ከተማ ከ85 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ የተደረሰበት ነዳጅ ማደያ መታሸጉን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሀላፊ ወይዘሮ ምስጋና በራሶ እንደገለጹት የነዳጅ ማደያው የታሸገው በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት በተደረገው ክትትል ቤንዚን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ሲሸጥ ተደርሶበት ነው።
ለሽያጭ የቀረበው ቤንዚን የጥራት ደረጃውን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ተልኮ በተደረገው ማጣራት የጥራት ጉድለት እንደነበረበት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በዚህም የነዳጅ ማደያው ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት በመፈጸሙ መታሸጉን ገልጸው፤ በህግ እንደሚጠየቅም አስታውቀዋል።
የወናጎ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስንታየሁ ጎሎ በከተማው እየተበራከተ የመጣውን ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ እንዲሁም ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ህብረተሰቡ በየደረጃው ከሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ህገ-ወጥነትን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ስንታየሁ ጠይቀዋል።