ሀዋሳን የጤናና የስፖርት እንቅስቃሴ ማዕከል ለማድረግ ይሰራል

106

ሀዋሳ ሰኔ 19/2014 (ኢዜአ) የሀዋሳ ከተማን የጤናና የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ተናገሩ ፡፡

በሀዋሳ የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም የብስክሌትና እግር ጉዞ መርሃግብር የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት ስፖርታዊ እንቅስቃሴውና ጉዞው በየሳምንቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ልማዱም ዳብሮና ባህል ሆኖ የከተማው ህብረተሰብ የጤና ሁኔታ ትርጉም ባለው መልኩ እንዲሻሻልም በአረንጓዴነቷ በምትታወቀው ሀዋሳ በስፋት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

የትራፊክ መጨናነቅና ከተሸከርካሪ የሚወጣ በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስም ሀዋሳን ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ እንደሚያስፈልጋትም ነው ያስረዱት፡፡

ከተማዋን የጤናና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባው፤ ለዚህም ለብስክሌትና እግረኞች ብቻ የሚሆኑ መንገዶችን የመገንባት ሥራዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል ፡፡

የከተማዋን መንገዶች የማስፋትና ከፕላን ውጪ ያሉ ሕገ-ወጥ ግንባታዎችን የማንሳት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የገለጹት ከንቲባው፤ ህዝቡም መሰል ጤናማ እንቅስቃሴዎችን እንዲያዘወትር ጥሪ አቅርበዋል።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዳነ አየለ በበኩላቸው ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ መርሃ ግብር መደረጉን አስታውሰው በሳምንት አንድ ቀን የተወሰኑ መንገዶችን ከተሸከርካሪ ነፃ በማድረግ ለእግረኛና ለብስክሌት ክፍት የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላልብለዋል፡፡

ከእግር ጉዞው ተሳታፊዎች መካከል የሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የአሰልጣኞች ቡድን አባል ጴጥሮስ ኤልያስ አንድ ሰው ጤንነቱን በሚገባ ለመጠበቅ በትንሹ በቀን 10 ሺህ እርምጃዎችን በእግሩ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አስረድቷል፡፡

በህብረተሰቡ ዘንድ ይህ እንቅስቃሴ እንዲዘወተር ደግሞ የዚህ አይነቱ መርሃግብር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደሆነም ነው የገለፀው፡፡

በብስክሌት ጉዞ የተሳተፈው ወጣት በኃይሉ ጌታቸው በበኩሉ በትንሹ ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ለግል ጤናችን ጊዜ በመስጠት በብስክሌትና በእግር የመጓዝ ባህልን ማሳደግ ይኖርብናል ነው ያለው፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለብስክሌትና እግረኞቸ ብቻ የሚሆኑ መንገዶችን ለመገንባት የጀመረው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ገልፆ፤ ከተማዋን ካደጉት ሀገራት ከተሞች ተርታ የሚያሰልፋት ጥሩ ጅምር ነውም ብሏል፡፡

በከተማዋ የሚከናወኑ መሰል የልማት ሥራዎችን መደገፍ ከሁሉም ነዋሪዎች እንደሚጠበቅም አመልክቷል ፡፡

በመርሃ-ግብሩ ከንቲባውን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የስፖርት ክለቦች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም