ህገ ወጥ የታሪፍ ጭማሪ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ዳርጎናል-የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች

83

ዲላ ሰኔ 19/2014 (ኢዜአ) በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ያለ በቂ ምክንያት በሚደረግ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረግን ነው ሲሉ በደቡብ ክልል የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።

የዞኑ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ በበኩሉ የነዋሪዎች ተባባሪ ያለመሆን የቁጥጥር ስራው ስኬታማ እንዳይሆንና ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዞኑ የቡሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ ወርቃለማ ሰብስቤ ለኢዜአ እንዳሉት 27 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከቡሌ ዲላ መንገድ 30 ብር የነበረው ታሪፍ ከቀናት በፊት በተደረገ የታሪፍ ማሻሻያ 50 ብር መግባቱን ጠቅሰዋል።

ይሁንና በመስመሩ ነዳጅ ተወዷል በሚል ሰበብ ከተሻሻለው ታሪፍ ከእጥፍ በላይ ለመክፈል እየተገደዱ መሆናቸውን ገልጸው ከዚህም ባለፈ ከወንበር በላይ ሰው እንደሚጫን ተናግረዋል።

ይህም ከመንገዱ የጥራት ችግር ጋር ተዳምሮ ለተጨማሪ ወጭና ህመም እየዳረጋቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ችግራቸውን እንዲፈታ ጠይቀዋል።

ከ60 ኪሎሜትር በላይ የሚሸፍነው ዲላ- ቡሌ- ሶላሞ መንገድም ተመሳሳይ ችግር እንዳለበት የሚያነሱት ደግሞ አቶ አባባየሁ መምህሩ ናቸው።

በተለይ የነዳጅ ውድነትንና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የታርፍ ጭማሪ ቢደረግም ተሽከርካሪዎች ከወንበር በላይ ሰው በሰው ላይ ደራርበው እንደሚጭኑ ተናግረዋል።

ከዲላ- ቡሌ- ሶላሞ መስመር ከጠጠር መንገድ ወደ ኮንክሪት አስፋልት ይቀየራል ተብሎ በተደጋጋሚ በፌዴራል መንግስት ቃል ቢገባም እስካሁን ድረስ አለመተግበሩ ችግሩን እንዳባባሰውም አስረድተዋል ።

በዚህም "በከፍተኛ ሁኔታ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረግን በመሆኑ የሚመለከተው አካል ቁጥጥር በማድረግ መፍትሄ እንድያበጅ" ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ የይርጋጨፌ ወረዳ ነዋሪ አቶ አረጋ ጸጋዬ ከዲላ ይርጋጨፌ አዲስ የወጣው ታረፍ 35 ብር ቢሆንም 50 ብርና ከዚያ በላይ ክፍያ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል ።

"የተጋነነ ታሪፍ ለመክፍል ካልተስማማን አያሳፍሩንም" ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ይህም እሳቸውን ለመሰለ በየእለቱ ትራንስፖርት ለሚጠቀም ዜጋ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው አመልክተዋል።

አዲሱ ታሪፍ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ እንዲሁም የባለንብረቶችን ተጠቃሚነት ከግምት ያስገባ ነው የሚሉት ደግሞ የቡሌ ወረዳ መንገድ ልማትና  ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይመር ታደሰ ናቸው።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ህገወጥ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ ህብረተሰቡ ላይ ጫና የሚያሳደሩ አሽከርካሪዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ይህንንም ለማስተካከል ከፖሊስ መዋቅር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጌዴኦ ዞን መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳዊት ቡነ በበኩላቸው ከነዋሪዎቹ  የተነሳው ቅሬታ ትክክል መሆኑን አምነዋል።

ይሁንና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በተጠቀሱት መንገዶች ላይ በሚሰሩ አሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህ ግን የበለጠ ውጤታማ የሚሆነው ህብረተሰቡ ተባባሪ ሲሆን ነው ብለዋል።

በተለይ የትራፊክ ፍሰትና የመንገድ ተቆጣጣሪዎች በጥቆማ ደርሰው ሲጠየቁ ተሳፋሪዎቹ የከፈሉትን ሳይሆን በትኬት ላይ የተጻፈውን መናገራቸው ችግሩን ያባብሳል ብለዋል።

የዚህን ችግር በጥናት ላይ በመመስረት እንዲሁም ማህበረሰቡን በማሳተፍ ለመፍታት የተቀናጀ አሰራር ለመዘርጋት ጥረት መጀመሩንም አቶ አቶ ዳዊት አመላክተዋል።

ችግሩን በአስተማሪ እርምጃ በዘላቂነት ለመፍታት የቁጥጥር ስራውን ውጤታማነት የሚያሳልጥ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማህበራትና ማህበረሰብ ያሳተፈ አደረጃጀት ለመፍጠር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ነው ያብራሩት።

በመሆኑም ህብረተሰቡ የተቆጣጣሪ አባላት በሚጠይቁበት ጊዜ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ህገወጦችን ማጋለጥ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት ።

ከተፈቀደው ውጭ ትርፍ ሰዎች ደራርቦ መጫን በትራፊክ ህግ ጥሰት ከሚወሰድ እርምጃ ባሻገር ለትራፍክ አደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑም አሽከርካረዎችና ባለንብረቶች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም