ወጣቶች ሀገራዊ ጉዳዮችን በመገንዘብ ለችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን ይገባቸዋል

46

ሰኔ 19 ቀን 2014(ኢዜአ)ወጣቶች ሀገራዊ ጉዳዮችን በመገንዘብ ለችግሮች የመፍትሄ አካል መሆን እንደሚገባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

"የእኛ ዘመን ወጣቶች ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ ፈተናዎችን ለመሻገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች የወጣቶችን አዎንታዊ ሚና ማጎልበት ላይ ያለመ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ባርዱላ ኦልከቦ በዚሁ ጊዜ ወጣቱ ወቅታዊ ሀገራዊ ችግሮችን በአግባቡ ተረድቶ ነገውን ለማጨለም እየተሰሩ ያሉ ሴራዎችን በመመከት ሀገርንና ህዝብን የመጠበቅ ሚናውን እንዲወጣ መድረኩ መመቻቸቱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን የውስጥና የውጭ ጫና ለመቋቋም ወጣቱ አቅሙን እያጎለበተ እንዲመጣ ተሳትፎው ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች የሴራዎች ድምር ውጤቶች መሆናቸውን በመረዳት ወጣቱ ለችግሮች ጣት የሚቀስር ሳይሆን የመፍትሄ አካል ለመሆን እንዲሰራም አሳስበዋል።

በብሔርና ሃይማኖት ሊከፋፍሉ ከሚሹ የጥፋት ኃይሎች ራስን መከላከል ይገባል ያሉት ሃላፊው፤የጠላት አካሄድ ለሀገርና ህዝብ የማይጠቅም መሆኑን በመረዳት መታገል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ጌራ በርናባስ በበኩሉ ኢትዮጵያ ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ "ጠንካራ የሥራ ባህልንና መደጋገፍን የሚጠይቅ ነው" ይላል።

ለችግሮች መስፋፋት መንስኤ እየሆነ ያለው በአቋራጭ ለመክበር የሚደረግ የስነ ምግባር ጉድለት የወለደው ሙስናና ተያያዥ ጉዳዮች የወለዱት ድርጊት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ወጣቱ አሁን ሳይደክሙና ሳይለፉ መጠቀም የሚቻልበት ጊዜ አለመሆኑንና ውጤቱም እርባና ቢስ መሆኑን ተረድቶ ያሉትን አማራጮች በሙሉ ተጠቅሞ ወደ ልማት መግባት ይገባል ብሏል።

"ለነገዋ የተሻለች ኢትዮጵያ ዛሬ የሚታየውን ችግር እንደመሰናክል ሳይሆን እንደመሸጋገርያ ድልድይ ተጠቅመን እንደምንሻገር እምነትና ተስፋ ልንይዝ ይገባልም ነው ያለው።

ለዚህም ወጣቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በመረዳት፣ ዙሪያ ገባውን ማየትና መመርመር፣ከስሜታዊነት መራቅ ሰከን ብሎ ማሰብ፣እንዲሁም የአባቶችን ታሪክ በመጠየቅ ሀገር የመገንባት ኃላፊነቱን ማወቅ አለበት ነው ያለው።

"ሀገራዊ ችግሮች ቢበዙም ተስፋዎቻችን ከዚያ በላይ ናቸው" የሚለው ደግሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ጌታቸው ባይባ ነው።

በወንድማማችነት መንፈስ ከሁሉም ጋር በሰላም የመኖር እሴቶችን በማንጸባረቅ አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ሲልም ተናግሯል።

መንግስት በሁሉም አካባቢ ፍትሃዊነትን በማስፈን የዜጎችን እኩል የመልማት ፤ዕኩል የመዳኘት መብት እንዲያስጠብቅም ጠይቋል ወጣቱ።

ሌላው ተሳታፊ ወጣት ታጋይ ሳፒ በበኩሉ ሰላም ከምንም ስለሚበልጥ ለሰላም ዋጋ ሰጥተን እንጠብቃለን ብሏል።

ወጣቱ በሥራ እጦት ምክንያት አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ እንዳይገባ መንግስትም የሥራ ዕድል መፍጠር እንዳለበት ጠይቋል።

በሚዛን ከተማ በተካሄደው የወጣቶች የውይይት መድረክ የከተማዋ ወጣቶችና የየወረዳዎቹ ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን በአካባቢያቸው ሰላምና አንድነት ላይ በትኩረት ለመስራት በመግባባት አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም