የሶማሌ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ላይ የፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አወገዘ

92

ጅግጅጋ ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በጥብቅ እንደሚያወግዝ የሶማሌ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታወቀ።


የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሼህ አህመድ አቢ፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሰሞኑን በንጹሃን ላይ አሸባሪው በፈፀመው አሰቃቂ ድርጊት በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።


የአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ተግባር በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለውና በጥብቅ እንደሚያወግዙም ነው ያስታወቁት።


መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለህግ እንዲያቀርብ እና ተጎጂዎችን እንዲያቋቋም በምክር ቤቱ ስም ጠይቀዋል ።


በክልሉ የሃይማኖት አባት የሆኑት ሼህ አብዲራህማን አሊ፤ አሸባሪዎች በማን አለብኝነት ህጻናትን ጨምሮ በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈፀሙት የጥፋት ተግባር በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።


ኡጋዝ አህመድ መሀሙድ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ቡድን ንጹሃንን እና አቅመ ደካሞች መግደሉ የሚያስኮንን አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።


"እንዲህ ዓይነት ወንጀል የሚፈፀሙ አካላትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህዝቡ በአንድነት በመቆም አሸባሪዎችን መታገል አስፈላጊ ነው ፤ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ በንጹሃን ዜጎች የተፈጸመውን ግድያ ሁላችንም ያሳዛነ ነውር ተግባር ነው " ብለዋል ኡጋዝ አህመድ።


መንግስት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ግድያና መፈናቀል ለማስቆም እየወሰደ ያለው እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።


መንግስት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት የፈጸመውን አሸባሪው የሸኔ ቡድንን ለመቆጣጠር እየወሰደ ካለው እርምጃ በተጓዳኝ ተጎጂዎችን ለመርዳት እየተረባረበ መሆኑን ቀደም ብሎ ተገልጿል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም