የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ማዕከላት የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክረው ይቀጥላሉ

172

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመከላከያ የትምህርትና ስልጠና ማዕከላት የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ፡፡

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ አባል በሆኑት ዶክተር ስራው ደማስ የተዘጋጀው "በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሚና" በሚል የደረሱት መጽሃፍ ተመርቋል።

በመርሀ ግብሩ የባህር ሃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ፣ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደመቀ መንግስቱ እንዲሁም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ ስርዓቶች ለአገር ያበረከተውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ የሚዳስሰው ይሄው መጽሐፍ በ360 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ለህትመት ለማብቃትም አራት ዓመታትን ወስዷል፡፡

የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ፤ መጽሐፉ ለመከላከያ ሰራዊት ግንባታ እንደ አንድ አጋዥ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል፣የትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጥናትና ምርምር በማድረግ የመከላከያን አቅም መገንባትና በየደረጃው ያሉ የሰራዊት አባላትን በእውቀትና በክህሎት ማብቃት መሆኑን ገልጸዋል።

መጽሐፍም ኮሌጁ ከተቋቋመበት አላማ አንፃር ትልቅ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም አዳዲስ እሳቤና ዕውቀት በማጎልበት ከአገራዊ ሁኔታዎች ጋር በማገናኘት ለጠንካራ ሰራዊት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደመቀ መንግስቱ በበኩላቸው ተቋሙ ለመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ትምህርትና ስልጠና ከመስጠት ጎን ለጎን የምርምር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መጽሐፉ የመከላከያ ሰራዊት ለጀመረው ሙያዊ ሰራዊት ግንባታ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ ለትምህርትና ተሞክሮ የሚሆኑ ሌሎች ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

በኮሌጁ የጥናትና ምርምር አስተባባሪና የመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር ስራው ደማስ፤ መጽሐፉ በሕብረተሰቡና በሰራዊቱ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጎለብታል ብለዋል፡፡በመከላከያ ሰራዊት ደረጃ እንደ አንድ የግንባታ መጽሀፍ እንዲሆን ታምኖበት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም