በአዲሱ ዓመት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚሰሩበት ዓመት መሆን አለበት

114
አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 አዲሱ ዓመት በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚሰሩበት ዘመን መሆን እንዳለበት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር ተናገሩ። የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ አሚን ጁዲ እንዳሉት፤ በአዲሱ ዓመት በመደመር ጥሪ የተሰባሰቡ የፖለቲካ ድርጅቶች በ2011 ዓመት ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት የሚሰሩበት ዘመን መሆን አለበት። በ2010 ዓመት በውጭ አገር የሚኖሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገር ጥላ ስር በሰላምና አንድነት ያሰባሰበ ዓመት በመሆኑ ሁሉም ለአገር ዕድገት በጋራ ለመሥራት ተሰልፏል ብለዋል። "ኢትዮጵያ ከነበረችበት ብዙ እዳዎች ወጥታ ወደ አዲስ ጎዳና እየተራመደች ነው ብለን ነው እምንገምተው። ይሄ አዲሱ ዓመት ደግሞ ለዚህ ፈር የቀደደ ነው። እኛም በውጭ የነበርነው ተቃዋሚ ኃይሎችም በአገር ውስጥ ያሉት እስር ቤትም የነበሩት፣ ሁሉም ለአንድ ኢትዮጵያ ዛሬ ለጋራ ለዴሞክራሲ ለሰላም ለመረጋጋት አብሮ የቆመ ነው የሚመስለኝ። ይሄ የተከፈተው እድል ደግሞ ይበልጥኑ ሰፍቶ ሰላማዊ አገር የሚቀይር ወደ እድገትና ወደ ሰላም የምንዛወርበት ዘመን እንዲሆን ነው የምመኘው። ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ነው፤ በቆንጆ ጊዜ ነው የመጣነው። ያለፉትን ዓመት የነበሩትን ሁሉንም ይቅር ብለን ወደ አዲስ ዓመት ስንመጣ የመደመሩም ጥያቄ ሲመጣ ከነበሩትም ጋር ወደ አንድነት መንገድ የምንመጣበት ዓመት ያድርግልን።" ''በአንድ አገር ዴሞክራሲ ለመገንባት ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው'' ያሉት አቶ አሚን፤ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን የተከተለ የፖሊስና ደህንነት ስርዓት በመዘርጋት ከህዝቡ ጋር በትብብር መስራት የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። ''ወቅቱ ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ ግፍና ጭቆናዎች የምናወራበት ሳይሆን ቂምና ቅራኔ በማስወገድ በህዝቦች መካከል ፍቅር እንዲሰፍን የምንሰራበት ነው'' ብለዋል። የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት የሚቻለው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር በመሆኑ የፓርቲው ደጋፊዎች ከሌሎች ህዝቦች ጋር የነበራቸውን ፍቅርና አብሮነት በማስቀጠል ለአገር ሰላምና ዕድገት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። "ዴሞክራሲን ለማስፈን ሰላምና መረጋጋት ዋነኛ ጉዳይ ነው። ይሄ አገር እንደ አገር አለ። አገሪቱ ደግሞ ህገ መንግስት አላት። አሁንም ህገ መንግስት ጠፍቶ ሳይሆን ህገ መንግስቱን በስርዓት ያለመተግበር፤ የደህንነት የፖሊስ ሁሉም ተቋማት የራሳቸውን ስርዓት በማውጣት ትክክለኛ መንገድ ባለመከተላቸው ነው። ህዝቡ ከፖሊሱ ጋር ነው፤ ከስርዓቱ በመተባበር የአገርን ደህንነት በመጠበቅ በህዝቦች መካከል ያለውን ያለመረጋጋት ማስከን፣ ፍቅር በፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በህዝብ መካከል እንዲሰፍን  የማድረግ ስራ፣ ከቅራኔ፣ ከቂም፣ ከነበሩት ስርዓቶች ማለትም ካለፉት ስርዓቶች አገዛዝ ስር ብዙ ግፎች፣ ብዙ ጭቆናዎች ተደርገዋል። አሁን እሱን እምናወራበት ጊዜ ሳይሆን የምንረጋጋበት ጊዜ ነው፤ ሰላም የምንፈጥርበት ጊዜ ነው። ስለዚህ ባለፈው ታሪክ ከመኖር አሁን ያለውን ጉዳይ በመገንዘብ ልናደርገው ወደምንችለው መንገድ ብንቀይሰው የሚሻል ነው የሚመስለኝ። ስለዚህ የአገራችንን ሰላም እናውርድ፤ ሰላም ካለ ዴሞክራሲ መፍጠር ይቻላል።" አዲሱ 2011 ዓመት የዴሞክራሲ ስርዓት የሚገነባበት፣ ሰላምና አንድነት የሚሰፍንበት ዓመት እንዲሆን አቶ አሚን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም