በሀላባ ዞን ከበልግ እርሻ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በሀላባ ዞን ከበልግ እርሻ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

ሀዋሳ፣ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀላባ ዞን በዘንድሮው በልግ እርሻ እየለማ ከሚገኘው 37 ሺህ ሄክታር መሬት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ሮባ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ በልግ በዘር ከተሸፈነው ከ39 ሺህ 210 ሄክታር መሬት ውስጥ 75 በመቶው የሚሆነው በኩታ ገጠም እየለማ ይገኛል።
ለበልግ አዝመራው ከ25 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ግብዓት አርሶ አደሩ እንዲጠቀም መደረጉን የገለጹት አቶ ሁሴን፤ 65 በመቶ የሚሆነው ማሳ በበቆሎ ሰብል መልማቱን ተናግረዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ በመጠቀምና 17 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየለማ የሚገኝ ነው ብለዋል።
እየለማ ከሚገኘው ሰብል ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ በማሳው ውስጥ ለሰብሉ ክትትል በማድረግ ከተምችና ከአረም በመጠበቅ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የዌራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሀመድ ኑርዬ በበኩላቸው በአከባቢው በአብዘኛው ልማቱ የሚካሄደው በበልግ ወቅት በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የተግባር ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ 12 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።