በ10 ወራት ለ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ተፈጥሯል

145

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ10 ወራት ለ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የዜጎች ስራ አጥነት ችግር እንዲፈታ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ሪፎርም የማድረግ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው ይኸም በርካታ ዜጎች የሙያ ስልጠና አግኝተው ወደ ስራ እንዲሰማሩ የሚረዳ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ባለፉት አስር ወራት ለ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል ሲፈጠር በርካቶችም ጊዜያዊ የስራ አድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

በአገር ውስጥ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች በተጨማሪ ከ54 ሺህ በላይ ዜጎች በውጪ አገራት የስራ ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።  

ለዜጎች ስልጠና በመስጠት ወደ ውጪ አገራት በመላክ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ቀጣይነት እንደሚኖረውም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።  

የስራ አጥነት ችግር አሁንም በቅጡ ያልተፈታ መሆኑን ጠቁመው ቀጣይም በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም