የዓለም ባንክ በምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም የ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ይፋ አደረገ

27

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም ባንክ በምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ እየተባባሰ የመጣውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ እና ማዳጋስካር በዓለም ባንክ ይፋ በተደረገው 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፓኬጅ ተጠቃሚ በመሆን ቀዳሚ አገራት እንደሚሆኑ የ ዘኔሽን መረጃ ያመለክታል።

ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ የሆነው ይኸው መርሃ ግብር ለዘጠኝ ዓመታት የሚቆይ ሁለገብ ድጋፍ ሲሆን በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ እየተባባሰ የመጣውን የምግብ ዋስትናን ችግር ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ለኢትዮጵያ 600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበ ሲሆን ለማዳጋስካር 158 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተመድቧል።

በመርሃ ግብሩ ሙሉ ዕዳውን በ38 ዓመታት የቆይታ ጊዜ እና በ6 ዓመት የእፎይታ ጊዜ ተለይቶ በሚታወቀው የዓለም አቀፍ ልማት ማህበር መደበኛ ውሎች የሚከፈል እንደሆነም ባንኩ አመልክቷል።

በዓለም ባንክ የግብርና እና የምግብ ዋስትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶክተር ሆልገር ክሬይ እንደገለጹት የሚሰጠው ገንዘብ እንደ አገሪቱ ሁኔታ በድጋፍ ወይም በብድር መልክ ይሆናል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ከሚሰጠው 788 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ 39 በመቶው በድጋፍ መልክ የሚሰጥ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በብድር የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ገንዘብ ውስጥ ሁለት ሶስተኛ ብድር ሲሆን ቀሪው በድጋፍ መልክ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መርሃ ግብሩ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እያሳየ ካለው ተጽእኖ አኳያ ተመዝኖ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግ በድጋሚ ለማረጋገጥ ያለመ ነው ተብሏል።

የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የምግብ ዋስትና ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ባለፉት ዓመታት መጨመሩን የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም