በፍትሕ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሕብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

23

ሰኔ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፍትሕ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሕብረተሰቡን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሎች የፍትሕ አካላት ገለጹ፡፡

ሕብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ፍርድ ቤት፣ አቃቤ ሕግ፣ ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች የተቀናጀ ሥራ ወሳኝ ነው፡፡

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሎች የፍትሕ አካላት በዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሕብረሰተቡን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተወካይ ኮማንደር ያህያ አብዱልሱልጣን የፍትሕ አካላት የተቀናጀ ሥራ በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ለሚከናወኑ ሥራዎች የጎላ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

"የፍትህ አካላት የተጠናከረ ሥራ የሕብረሰተቡን የፍትሃዊነት ጥያቄ መመለስ ያስችላል" ያሉት ኮማንደር ያህያ፤ በፍትሕ ዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራትን ከሕብረተሰቡ ጋር መገምገማቸውን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ  አብዱልሰላም አህመድ የሕብረተሰቡን የፍትሕ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁሉን አሳታፊ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል፡፡

በቀጣይም በዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሚፈለገው መጠን ለመመለስና ተጠያቂነትን ለማስፈን በቅንጅት እንደሚሰሩም ነው ያነሱት፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሕግ ረቂቅ ጥናትና ምክር አቃቤ ሕግ ኮማንደር ይልማ ጥላሁን በበኩላቸው፤ በክልሉ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የፍትሃዊነት ጥያቄዎች ለመመለስና ክፍተቶችን ለማረም አራቱን የፍትሕ አካላት ያካተተ ፎረም ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በመልካም አስተዳደርና ሙስና፣ በሰብዓዊ መብትና ወንጀል-ነክ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት በፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በማረሚያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥና የሕዝብ እርካታን አስመልክቶ ያካሄደውን ሀገር አቀፍ ጥናት ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በጥናቱ  ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ  ጠንካራ የፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም ሁሉንም ሕብረተሰቡን ለእንግልትና ለብልሹ አሰራር ያጋለጡ ተግባራት መኖራቸው ተጠቅሷል።

በመሆኑም ተቋማቱ ራሳቸውን በመፈተሽ ለብልሹ አሰራር የሚያጋልጡ አሰራሮችን እንዲቀርፉና ፍትሕ ፈልጎ የሚመጣውን ሕብረተሰብ የሚያጉላሉ ሠራተኞች ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ በጥናቱ ምክረ- ሀሳብ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም