ቀጥታ፡

ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ሳይንሳዊ አሰራርና አደረጃጀትን መዘርጋት ይገባል -ዩኒቨርሲቲ

ደብረ ማርቆስ ፤ ሰኔ 16/2014 ኢዜአ) በአገሪቱ ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሳይንሳዊ አሰራርና አደረጃጀትን መዘርጋት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ የተመሰረተበትን 30ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ 2ኛውን ዙር ክልላዊ የጥናትና ምርምር አውደ ጥናት በደብር ማርቆስ ከተማ አካሂዷል።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጋሹ አለማየሁ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የፖሊስ አገልግሎት ወሳኝ ነው።

ዘመናዊ የፖሊስ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት ሳይንሳዊ አሰራርና አደረጃጀትን ፈጥሮ መንቀሳቀስ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

"ለዚህም ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተሞክሮዎችን አምጥቶ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም በየጊዜው የሚገነባ የፖሊስ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል" ብለዋል።

በዘርፉ ጥናትና ምርምር የሚቀርብበት መድረክ መዘጋጀቱ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለማረም ስለሚያስችል በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አንማው አለሜ በበኩላቸው፣ የፖሊስ ተግባር    ወንጀሎችን አስቀድሞ መከላከልና ሲከሰቱም በቀላሉ መቆጣጠር መሆኑን ተናግረዋል።

"በየጊዜው ስልት በመቀያየር  በሚፈጽሙት ወንጀል ህብረተሰቡን ሰላም የሚነሱ አካላትን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብም የፖሊስ ቁልፍ ተግባር ነው" ብለዋል።

ለዚህም ፖሊስን በየደረጃው በስልጠና፣ በአሰራርና በአደረጃጀት በማዘመን የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

የአውደ ጥናቱ ዓላማም በጥናታዊ ግኝቶች ላይ ተመስርቶ ድክመቶችን ለማረምና ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል መሆኑን ገልጸዋል።

መድረኩ ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ተግባራዊ የሚሆኑበትን ስልት ለመቀየስ የራሱ ጥቅም እንዳለው ተናግረዋል።

"በተጨማሪም የወንጀል መከላከልና የምርመራ ስልትን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማሳደግ የፖሊስ ተልዕኮን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ ነው" ብለዋል።

በመድረኩ ለፖሊስ አገልግሎት ማነቆ የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት ትኩረት እንዲሰጣሰቸው መፍትሄ አመላካች ጥናት ማቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ ኮማንደር አለነ ወንድማገኝ ናቸው።

በማንኛውም ጊዜ የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ የፖሊስ አገልግሎትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑንና ጥናታቸውም ይህንን ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ማመላከቱን ተናግረዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የጥናትና ምርምር ዓውደ ጥናት ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም