ቀጥታ፡

ኢዜአ እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሙያ ሥልጠናን ጨምሮ በሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ሰኔ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ / እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የሙያ ሥልጠናን ጨምሮ በሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዙሪያ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን  ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ  ዘሪሁን ተፈራ ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ተቋማቱ በሙያ ሥልጠና፣ የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በማቅረብ እና በማስተባበር፣ በመደጋገፍ፣ ትብብር በመፍጠርና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ከአንጋፋው የሚዲያ ተቋም ኢዜአ ጋር በጋራ መሥራት መልካም አጋጣሚ መሆኑን የገለጹት ሻለቃ ዘሪሁን፤ በተለይም ለፈጣንና አስተማማኝ የመረጃ ተደራሽነት ያግዘናል ብለዋል።

የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ለሕብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚሰራ ተቋም በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ኢዜአ ተጨማሪ አጋዥ በመሆኑ አመስግነዋል።

ከተማዋ በተለይም የወንጀል ጥሰቶች እንዳይከሰቱ፣ ለነዋሪዎቿና ለዲፕሎማቶች ጭምር ምቹና ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ባለሥልጣኑ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የባለሥልጣኑን ሥራዎች ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ ኢዜአ ከፍተኛ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የጋራ ስምምነቱ ደግሞ ለተሻለ ሥራ የሚያበቃ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢዜአ የዜና ሽፋን ከመስጠት ባሻገር ተቋሙ በሚሰራቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እገዛ በማድረግና ለተቋሙ የሚዲያ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ጭምር ተቋሙን የሚያግዝ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ባለሥልጣኑ የሚሰራቸው ሥራዎች ኢዜአ ከሚሰራቸው አገራዊ ሥራዎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ እድገት የአገሪቱ  እድገት በመሆኑ በዚህ ዙሪያ ባለሥልጣኑ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ኢዜአ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢዜአ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች ባሉት 38 ቅርንጫፎች የተለያዩ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ያለ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

ተቋሙ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ እያስገነባ ሲሆን ግዙፍ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስቱዲዮ ባለቤትም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም