የሀገር በቀል አምራቾችን ቁጥር ለመጨመርና የነባሮችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር በቀል አምራቾችን ቁጥር ለመጨመርና የነባሮችን የማምረት አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ነው
ሰኔ 16 ቀን 2014/ኢዜአ/ ለአምራች ዘርፉ ምቹ የአሰራር ስርዓትን ለመፍጠር፣ የሀገር በቀል አምራቾችን ቁጥር ለመጨመርና የነባሮችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ያዘጋጀው‹‹የሀገራችንን ምርት በመጠቀም ነጋችንን እንገንባ!” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽንና ባዛር በዛሬው እለት ተከፍቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ ለአምራች ዘርፉ ምቹ የአሰራር ስርዓትን ለመፍጠር፣ የሀገር በቀል አምራቾችን ቁጥር ለመጨመርና የነባሮችን የማምረት አቅም ለማሳደግና ተወዳዳሪ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዘርፉን የፋይናንስ እጥረት ለመፍታት በተለያዩ ተቋማት ተደራሽ የሚደረግ የሊዝ ፋይናንስና የስራ ማስኬጃ ብድር ተመቻችቶ ሲሰራ መቆቱን ገልፀው አምራች ኢንተርፕራይዞች የሚፈልጉትን የፋይናንስ ፍላጓት ከማሟላት አንጻር በቂ ባለመሆኑ የተለየ የድጋፍ አሰራር በቀጣይ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ጥናቶች ለመንግስት መቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
አምራች ኢንተርፕራይዞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን አቅምን ማሳደግ እንደሚስፈልግና ከዘርፉ አስፈፃሚና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠይቅ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
ከኤግዚቢሽንና ባዛሩ ጎን ለጎን የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የፕሮሞሽን መድረክ (side event) መዘጋጀቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይ በጀት ዓመት ብቃት ያላቸውን ኢንተርፕራይዞችን የመለየት፣ የመደገፍና የማዘጋጀት ስራ በመስራት በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲሳተፉና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አምራች ኢንተርፕራይዞች ተኪ ምርት እንዲያመርቱና በውጭ ገበያ በስፋት እንዲሰማሩ ለማስቻል ከተለያዩ መንግስታዊ፣ የግልና አጋር የልማት ተቋማት ጋር የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጠልም ተናግረዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሩም ከ227 በላይ የሚሆኑ በጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና ቆዳ ውጤቶች፣ በብረታ ብረት፣ እንጨት ሥራና የኢንጅነሪንግ ስራዎች፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግና በኬሚካል ውጤቶች፣ በቴክኖሎጂ ውጤቶችና ፈጠራ ስራዎች፣ የተሰማሩ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ሰጪና አጋር ተቋማት ይሳተፉበታል፡፡
ኤግዚቢሽንና ባዛሩ ሜክሲኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ፊት ለፊት የተዘጋጀ ሲሆን እስከ ሰኔ 23 እንደሚቆየና የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የፕሮሞሽን መድረክም መዘጋጀቱን ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡