ቀጥታ፡

ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ ተደረገ

ሰመራ፤ ሰኔ 16/2014 (ኢዜአ)፡ በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 600 ኩንታል የምግብ ዱቄት ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉ የተደረገው ግሎባል አልያንስ በአሜሪካ ከሚኖሩ ሀገር ወዳድ የድርጅቱ አባላት ባሰባሰበው ገንዘብ መሆኑ ተመላክቷል።

የግሎባል አልያንስ የኢትዮጵያ ተጠሪ አርቲስት ደሳለኝ ሃይሉ  ድጋፉን ለአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና ለአፋር ልማት ማህበር ሃላፊዎች ዛሬ አስረክበዋል።

አርቲስት ደሳለኝ በዚሁ ወቅት እንዳለው የአፋር ህዝብ  ሀገሩ በፈለገችው ወሳኝ ሰዓት ለሀገሩ ህልውና ዘብ የሚቆም ጽኑ ኢትዮጵያዊ ነው።

ለዚህም ''አሸባሪው ህወሓት  በሀገር ህልውና ላይ የጋረጠውን አደጋ  ለመቀልበስ የከፈለውን መስዋዕትነትና የሰራውን አኩሪ ገድል ማስታወስ በቂ ነው'' ብለዋል።

የአፋር ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እንደደረሰበት የተናገረው አርቲስት ደሳለኝ፤
ድጋፉ በአሜሪካ በሚኖሩ ሀገር ወዳድ የድርጅቱ አባላት  መደረጉን ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮች የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ  ዲያስፖራውን በማስተባበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ህይወት  በእርዳታ ላይ እንዲመሰረት ማስገደዱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ይጠቀምባቸው የነበሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትም መውደማቸውምን ጠቁመዋል።

ለተፈናቃዮቹ የእለት ደራሽ እርዳታ ማቅረብና የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባት በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል አለመሆኑን ጠቁመው፤ ''ለዚህም የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ ወሳኝ ነው'' ብለዋል።

ድርጅቱ ለክልሉ ተፈናቃዮች ሁለት ጊዜ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ላበረከተው ድጋፍ በተጎጂ ወገኖች ስም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም