ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የሚመጥን አዲስ አገራዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የሚመጥን አዲስ አገራዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል

ሰኔ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የሚመጥን አዲስ አገራዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
ከዛሬ 4 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ስር የሰደደ የኢኮኖሚ ስብራትና ኢ-ፍትሃዊነት ያየለበት፣የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና አፈና የነገሰበት፣ጥቂቶች በቡድን ተደራጅተው የሚፈነጩበት ሕወሃት መራሹ ስርዓት በህዝብ ትግል ተለውጧል።
አገራዊ ለውጡ የተከበረችና የታፈረች፣ዜጎቿን በዕኩልነት ያሰባሰበች ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን በሚገነባና ኢትዮጵያን በሚያፈርስ ቡድን መሃል ግብግብ ገጥሞታል።
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላቱ ዶክተር አለሙ ስሜ፣ ዶክተር ሰማ ጥሩነህ፤ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እና አቶ ርስቱ ይርዳው ፤በሕዝብ መራር ተጋድሎ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከለውጡ መባቻ ጀምሮ እልህ አስጨራሽ ትግል እንደተደረገ ያወሳሉ።

በተለይም አሸባሪው ቡድን ሕወሃት በተዛባ ትርክት ክፍፍልና ጥርጣሬን ማናር፣የማህበራዊ እሴቶች ተጋምዶን መናድ፣በብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች ህዝብን ማማረር በመጨረሻም ግልጽ ጦርነት በማወጅ አገርን ማፍረስ ላይ ሌት ተቀን ሰርቷል።
ከውስጣዊና ውጫዊ ሰው ሰራሽ ችግሮች ባለፈ በኮቪድ 19፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ጎርፍና ድርቅ መሰል ተፈጥሯዊ ችግሮችም ክፉኛ እንደተፈተነ አስታውሰዋል።
በፈተናዎች የታጀበው አገራዊ ልውጥ የተሰደዱ እንዲመለሱ፣የታሰሩት እንዲፈቱ፣የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ፣የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡና አሳሪ ሕግጋት እንዲሻሻሉ በማድረግ የዴሞክራሲ መሰረት ጥሏል።

ድሕረ አገራዊ ለውጡ ቤተኛ እና ተመልካች ሳይኖር ሁሉም የሚሳተፉበት መንግስታዊ ስርዓት ስለመመስረቱ ያነሳሉ።
የቀደመ የሴራ፣የወዳጅና ጠላት ፖለቲካ የጋራ አገር በጋራ የመስራት መንፈስ የተተካበት፣በነፃና ዴሞከራሲያዊ ምርጫ ህዝባዊ መንግስት የተመሰረተበት፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተሳካ መልኩ የተከናወኑበትና ጤናማ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ዕውን መሆን የተጀመረበት ለውጥ ነው ይላሉ።
የለውጡ ምክንያት የሆኑ አገራዊ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራቶችን በመጠገን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የመውሰድ የአንኳር ዓላማ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለውጡ የወለደው ብልጽግና ፓርቲም ያለፉ ህፀጾችን በማረም፣በጎዎችን በማዳበር ኢትዮጵያን የሚመስል ብልጽግና ማረጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመትከል ግብ ይዞ እንደተመሰረተ ገልጸዋል።
የፓርቲው አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ቅቡልነት ያለው፣ሁሉንም ህዝቦች የወከለ ህብረ ብሄራዊና ወጥ፣የተደራጀና ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
ጉባዔው አገራዊ ለውጡ ስኬቶቹን እየገመገመ የተራመደ፣የፈተናዎችን ምንጭና መፍትሄ ለይቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ ታሪካዊ ጉባዔ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባዔው በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ በመላ አገሪቷ ህዝባዊ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎቹ ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ ስለመሆኑ ተረጋግጦ ወደ ስራ መገባቱንም አንስተዋል።
በዚህም የህዝብ ጥያቄ የሆነውን ሕግ ማስከበር፣የአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ችግሮች፣የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ማህበራዊ ችግሮች መፍታት ላይ ማተኮሩን አስታውሰዋል።
በዚህም በሕግ ማስክበር ስራው በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልልች በጸረ ሰላም ሃይላት ላይ በተወሰደ እርምጃ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት መረጋገጡን፣የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ በንጹሃን ላይ የጅምላ ግድያ በፈፀመው የሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ መንግስት የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው በቀጣይም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ፣ሙስናን የመታገልና የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በፖለቲካው መስክ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ወደ ኋላ ያስቀሩ የፖለቲካ ባህልን በማስቀረት ታፋሪና ተከባሪ የሚያደርግ አዲስ አገራዊ አስተሳስብ እውን ይሆናልም ብለዋል፡፡

ብዝሃነትን፣ሕብረ ብሔራዊነትና ሚዛናዊነትን የተቀበለ፣በፍትሃዊነትና እኩልነት መርህ የሚመራ፣ለዜጎች መብት ቅድሚያ የሚሰጥና የአገር በቀል እሴቶችን ያካተተ ስርዓት መገንባት ላይ እንደሚተኮር ገልጸዋል።
ውስጠ ዴሞክራሲ ማጎልበት፣በትምህርትና ስልጠና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የሰለጠነ የሰው ሃይል መገንባት፣በማህበራዊ ልማት የጀመራቸውን አመርቂ ውጤቶች ማስፋት የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ነው ብለዋል።
በአገራዊ አካታች ምክክር የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲሰጥ ብልጽግና አቅጣጫ ማስቀመጡን የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላቱ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፣ አቶ ርስቱ ይርዳውና ዶክተር ሰማ ጥሩነህ ገልጸዋል።
በየወቅቱ በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳይበገር እንደሚሰራ ገልፀው ህዝቡ ከፓርቲው ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።