ቀጥታ፡

በክልሉ ባህላዊ ወርቅ አምራቾችን ከባለሀብቶች ጋር ለማቀናጀት የተሰራው ስራ ውጤት አስገኝቷል

አሶሳ፤ ሰኔ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት የባህላዊ ወርቅ አምራቾችን ከባለሀብቶች ጋር ለማቀናጀት የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ ናስር መሐመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ኤጀንሲው የክልሉን ማዕድን በአግባቡ  ለማልማት የአሰራር ማሻሻያ አድርጓል፡፡

 ባህላዊ ወርቅ አምራቾችን ከባለሀብቶች ጋር ለማቀናጀት በትኩረት መሰራቱን አመልክተው፤ በዘርፉ የተከናወነው ስራ የወርቅ ምርት በስፋት ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማስቻሉን ጠቁመዋል፡፡

 ለ192 ወርቅ አምራች ማህበራት ዘመናዊ የወርቅ መሳሪያዎች አቅርቦት መደረጉን አመልክተው፤ በማህበራቱ የጥራት ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ አቅማቸውን የማጠናከር ሥራ መከናወኑን አመልከተዋል።

በዘርፉ በተሰራው ሥራ በ2014 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከ2 ሺህ 200  ኩንታል በላይ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን አቶ ናስር አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ማህበራትን በፋናንስና በቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችል “ቤጉ ዴቨሎፕመንት” የተባለ የመንግስት የልማት ድርጅት ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ በዘርፉ ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ  ወርቅን ጨምሮ ከማዕድን ሀብት ታክስና ለባለመብት የሚከፈል ገንዘብ 44 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ህገ ወጥ የወርቅ ዝውውር የዘርፉ ዋነኛ ፈተና መሆኑን ጠቁመው፤ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ጠንካራ ስራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ በተለይ የባህላዊ ወርቅ አምራቾችን ግንዛቤ በማሳደግ ምርቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ ብቻ እንዲያስገቡ የማድረግ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በህገወጥ ወርቅ ማዘዋወር የተሰማሩ 19 ግለሰቦችን ፈቃድ በመንጠቅ በህግ ለመጠየቅ እንቅስቃሴ መጀመሩን  አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሶሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ወገኔ ጎርፌ በበኩላቸው ብሔራዊ ባንክ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰጠው ውክልና ቅርንጫፉ ከህጋዊ ወርቅ እምራቾች  ወርቅ እየተረከበ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ጥቁር ገበያ የሚገባውን ወርቅ ለመከላከል  ወደ ባንኩ ወርቅ የሚያመጡ አምራቾችም ሆኑ ህጋዊ አዘዋዋሪዎች አምስትና ከዚያ በላይ ኪሎ ግራም ወርቅ ሲያቀርቡ እስከ 29 በመቶ ተጨማሪ የማበረታቻ ክፍያ እንሚዲያገኙ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ፣ ካማሽና መተከል ዞኖች በሚገኙ 21 ወረዳዎች  ወርቅ ሀብት ክምችት በስፋት እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም