ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን የጭካኔ ድርጊት የሚያትተው “የተካደው የሰሜን ዕዝ” መፅሐፍ ሊተረክ ነው

ሰኔ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ)አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ የሀገር መካለከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን የጭካኔ ድርጊትና በሰራዊቱ የተመዘገበውን ድል የሚያትተው “የተካደው ሰሜን ዕዝ” መፅሐፍ በትረካ መልክ ሊቀርብ ነው።

ጥቅምት 24 በእለተ ማክሰኞ ለዚያውም በውድቅት ሌሊት ሰራዊቱ ሀገር አማን ብሎ በተኛበት አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገር ዘብ በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ የጭካኔ በትሩን አሳርፏል።

"ትረፊ ያላት ነፍስ" እንዲሉ ከጥቃቱ ተርፎ ሁነቱን ለመመስከር የበቃው ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው (ቻቻው) "የተካደው ሰሜን ዕዝ" በሚል ርዕስ የደረሰውን መጽሃፍ ለተደራሲያን እንካቹህ ማለቱ ይታወሳል።

የተካደው የሰሜን ዕዝ የታፋኙ ወጥቶ አደር ማስታዎሻ መጽኃፍም "የማይካደው" በሚል መሪ ቃል በአንጋፋው የኪነጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ ተተርኮ ለአድማጭ ተመልካቾች እንዲተላለፍ ተሰናድቷል።

የመፅሃፉን ትረካ በቀረፃና ቅንብር የሰነደው የኢትዮጵ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) መጽሃፉን ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ እንዲዘጋጅ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬሸን (ኢብኮ) የመጽሃፉን ትረካ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ተደራሽ ለማድረግ ሃላፊነት ወስዶ ተረክቧል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳኒኤል ክብረት፤ኢዜአ መጽሃፉን በትረካ መልክ ማዘጋጀቱ፤ኢብኮ ደግሞ እንዲተላለፍ ሃላፊነት መውሰዱን አመስግነዋል።

የመፅሐፉ መተረክ መጽሃፉን ማግኘት ላልቻሉ ወገኖች እንዲደርስ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የተካደው ሰሜን ዕዝ ማስታወሻ ደራሲ ሃምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው፤ መጽሃፉ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ "የማይካደው-ተካደ" በሚል መሪ ሃሳብ ለህትመት ከዚያም ተሻግሮ ለትረካ መብቃቱ እንዳስደሰተው ገልጿል።

ምንም እንኳን ከኃዲዎች የማይካደውን ቢክዱትም ወታደር በህልፈቱ ሀገርን ማስቀጠል በህይወቱ ደግሞ ህዝብን መጠበቅ የዘወትር ስራውና እርካታው ነው ብሏል።

የኢዜአ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፤ጠቅላይ ሚነስትር ዐብይ አሕመድ፤የኢዜአ 80ኛ ዓመት ላይ ተገኝተው ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም እውነተኛ መረጃ ማድረስ አለባችሁ በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት በመሰነቅ እውነተኛና ጠቃሚ መረጃ ለህዝብ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሃምሳ አለቃ ጋሻው ጤናው የደረሰው መጽሃፍም ለህዝቡ በሚጠቅም፤ የሰራዊቱን ክብር በሚመጥንና በሚያከብር መልኩ ተተርኮ መቅረቡን ተናግረዋል።

መጽሃፉ ለኢትዮጵያዊያን ትምህርት በሚሆን መልኩ ተቃኝቶ እንዲተላለፍ በማሰብ በትረካ መልክ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የኢብኮ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍስሃ ይታገሱ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው የግፍ ጥግ ለኢትዮጵያዊያን በሚገባው ልክ ተላልፎ ይሆን የሚለው የዘወትር ጥያቄያቸው እንደነበር ገልጸዋል።

መጽሃፉ በተከሰተው ታሪክ ውስጥ ተሳትፎ በነበረውና የግፍ ጽዋውንም በቀመሰው ወታደር የተፃፈ በመሆኑ ህዝብ እውነታውን በሚገባ እንዲረዳ ያስችላል ብለዋል፡፡

በመሆኑም ትረካው በተቋሙ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ማሰራጫዎች ለህዝቡ እንደሚተላለፍም አረጋግጠዋል፡፡

"የማይካደው" የተካደው ሰሜን ዕዝ መጽኃፍ ትረካም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን የሬዲዪና ቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢዎች የሚተላለፍ ሲሆን አድማጭ ተመልካቾች ትረካውን እንዲከታተሉ ከወዲሁ ተጋብዘዋል።

መጽሃፉ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ተመርቆ ለተደራሲያን መቅረቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም