በምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናችን ተረጋግተን ትምህርታችንን እንድንማር አስችሎናል---አስተያየት የሰጡ ተማሪዎች

80

ሰቆጣ ፤ ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ ) ''በትምህርት ቤት የምገባ መርሃ -ግብር ተጠቃሚ መሆናችን ተረጋግተን ትምህርታችን እንድንማር አስችሎናል'' ሲሉ በአማራ ክልል ዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተማሪዎች ተናገሩ።

በዞኑ በ176 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚማሩ ከ85 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።

በሰቆጣ ከተማ የአዝባ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ በላይኑ ጌታቸው እንዳለችው የምገባ መርሃ  ግብሩ ተጠቃሚ በመሆኗ ያለምንም ችግር ሙሉ ጊዜዋን በትምህርቷ ላይ እንድታደርግ አስችሏል።
በልቶና ሳይበላ ትምህርትን  በመከታተል ሂደት ላይ ልዩነት ያለው በመሆኑ የምገባ መርሃ ግብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች።

ከቤት ምግብ ሳንበላ ትምህርት ቤት ስንሄድ ትምህርት ለመከታተል እንቸገር ነበር የምትለው በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የቲያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሃይማኖት ደርበው ነች።

"አሁን በትምህርት ቤቱ በሚሰጠንን ምግብ ትምህርታችንን በአግባቡ እንድንከታተል አስችሎናል" ስትል ተናግራለች።

በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የቲያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስነ ምግብ ተጠሪና የስነ ህይወት መምህር ጊዜነው መኩሪያ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ ከመጋቢት ወር 2014 ጀምሮ መርሃ ግብሩ መጀመሩን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ 580 ተማሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ሆነው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ በመግለጽ።

መርሃ-ግብሩ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥና የማርፈድ ችግርን በመቅረፍ የትምህርት ቤቱን የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሻሻል ትልቅ ሚና ማበርከቱን አስታውቀዋል።

በዞኑ ትምህርት መምሪያ የትምህርት ቤቶች ምገባ አስተባባሪ አቶ ወንድሙ አየነው በበኩላቸው በአምስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር ከመጋቢት ወር 2014 ዓ/ም ጀምሮ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እየተተገበረ ይገኛል ብለዋለ።

በ176 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ 85 ሺህ 113 ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በብሄረሰብ አስተዳደሩ እየተካሄደ ያለውን የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ እስኩል ሜል ኢንሼቲቭ፣ የህፃናት አድን ድርጅትና በክልሉ ትምህርት ቢሮ አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

''መርሃ ግብሩ የአቋራጭ ተማሪዎችን ቁጥር እንዲቀንስ ከማድረጉ በተጨማሪ ህወሃት በከፈተው ጦርነት  ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በሁሉም ትምህርት ቤቶች በፍትሃዊነት ምገባው ተደራሽ እንዲሆን የተማሪ ወላጆች ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን መግለጻቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም