ከምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 25 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ተሰበሰበ

53

ሻሸመኔ/አምቦ ስኔ 15/14(ኢዜአ) ከምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚወል 25 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ። 

በሁለቱ ዞኖች ድጋፉ የተሰበሰበው እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት ውስጥ ነው።

የምዕራብ አርሲ ዞን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ለገሰ፤ የዞኑ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት ህዝቡን በማስተባበር ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመትም እንደ ዞን ከተለያየ ገቢ ምንጮች 18 ነጥብ 5 ሚሊዩን ብር  ለመሰብስብ ታቅዶ  እስከ አሁን 19 ነጥብ 7 ሚሊዩን ብር  ተሰብስቧል ብለዋል።

ከተሰበሰበው የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ  ባለ ሃብቶች 35 በመቶ፣ ነጋዴዎች 25 በመቶ፣ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች 40 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ለታለመለት ግብ እንዲውል ሁሉም የዞኑ ህብረተሰብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተባባሪዋ  ጠይቀዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ሰኔ 19/2014 ዓ.ም ከአርሲ ዞን ወደ ምዕራብ አርሲ ዞን የሚገባ በመሆኑ ለአቀባበሉ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተመልክቷል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን ለታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ወርቅነህ ሁንዴሳ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ  በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች በተደረገ እንቅስቃሴ ከተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዢና ስጦታ ከ5 ሚሊየን  ብር በላይ መሰብሰቡን ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህም ከተሰበሰበው ገቢ 978ሺህ ብር በስጦታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓመቱ ለማሰባሰብ የታቀደው ገቢ ለማሳካት ስራው መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

ግድቡ የሀገሪቱን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው የኅብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ቀን ጀምሮ በዞኑ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ሽያጭና በስጦታ 69 ሚሊየን  የሚጠጋ ብር መሰብሰቡን አስታውሰዋል።

ከዞኑ ሴክተር መስሪ ቤት ሰራተኛ መካከል አቶ ለታ ገመቹ በሰጡት አስተያየት፤ የ500 ብር የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ገልጸው፤ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል  የ1ሺህ ብር ቦንድ እንደገዙ የገለጹት  አቶ ምስጋናው ገመቹ በበኩላቸው፤ "የግድቡን ግንባታ አስጀምረን እንዳገባደድነው ማንም ሳያስቆመን እናስጨርሰዋለን" ብለዋል።

"ለግድቡ ግንባታ የሚደረግ ድጋፍ ራስን መደገፍ ማለት ስለሆነ በምችለው ሁሉ እደግፋለሁ" ያሉት ደግሞ የአምቦ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብዙአየሁ ዘሪሁን ናቸው፡፡ 

ለዘመናት የባዕዳንን ምድር ሲያጠጣ የኖረው ዓባይ ለአብራኩ ክፋዮች ግን የጎላ ሲሳይ አልነበረውም፤ ኢትዮጵያዊያን በቁጭት ተነሳስተው በራሳቸው ሃብት እና እውቀት ለሀገራቸው ልማት፤ ለጎረቤቶቻቸው ትሩፋት ለማድረግ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ  ጀምረው በመፈጸም ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም