በሀድያ ዞን በአንድ የግል ባለሀብት የተገነቡ አራት ድልድዮች ለአገልግሎት በቁ

133

ሆሳዕና፤ ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን ዱና ወረዳ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአንድ የግል ባለሀብት የተገነቡ አራት ድልድዮች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ።

የተለያዩ የገጠር ቀበሌያትን የሚያገናኙት ድልድዮች የተለያዩ የስራ ሃላፊዎችና የአከባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቀዋል።

 የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ሎምበሶ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የክልሉን  ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግል ባለሀብቶች ተሳትፎ የጎላ ነው።

የክልሉ መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ ''እንደዚህ አይነት መሰረት ልማቶች  መልካም አሳቢ በሆኑ ባለሀብቶች መገንባታቸው የሚበረታታ ነው ''ብለዋል።

ባለሀብቱ የአካባቢው ህብረተሰብ የዘመናት ጥያቄ ሆኖ የቆየው የመንገድና የድልድይ ችግር እንዲፈታ ላደረጉት አስተዋጽኦ ዋና አስተዳዳሪው አመስግነዋል።

ሌሎችም የግል ባለሀብቶች የባለሀብቱን አርያነት በመከተል ለክልሉ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የዱና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አበራ በበኩላቸው ''አካባቢው ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ በማህበረሰቡ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ባለሀብቱ በራስ ተነሳሽነት አራት ድልድዮች ገንብተው በማስረከባቸው ሊመሰገኑ ይገባል'' ብለዋል።

የድልድዮቹ ግንባታ በዱና ወረዳ ካሉ ቀበሌያት አስቸጋሪ መልከዓምድር ያላቸውና በክረምት ከፍተኛ ችግርና ስጋት የሚፈጥሩ የሰባት ቀበሌያት ችግር የፈታ መሆኑን ጠቁመዋል ።

ድልድዮቹ የተገነቡባቸው ሰሜን ዋገበታ፣ደቡብ ዋገበታ፣ሀኩፈናና ሄባና በርኩንቾ የተባሉ ቀበሌዎችን  ከከምባታ ጠምባሮ ዞን አጎራባች ወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ በመሆናቸው ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑን  አመላክተዋል።

''በተወለድኩበት አካባቢ የሚስተዋለው የመንገድና የድልድይ አለመኖር በወላድ እናቶችና በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያደርሰው እንግልት ከፍተኛ መሆኑ ድልድዮቹን ለማስገንባት አነሳስቶኛል'' ያሉት ደግሞ የግል ባለሀብቱ አቶ አዳምሰገድ ዱናሞ ናቸው።

ለድልድዮቹ ግንባታ ከ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጋቸውን ያስታወቁት ባለሀብቱ፤ ''ከህዝብ መጠቀም ብቻ ሳይሆን ህዝብን መጥቀምም ይገባል'' ብለዋል።

በቀጣይ የአከባቢውን  ተጠቃሚ የሚያደርጉ የችፑድ ፋብርካና የእህል ወፍጮ አገልግሎት ሥራ ለማስጀመር በዝግጅቱ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ በቀለ አቦዬ በበኩላቸው የዘመናት ጥያቄ የነበረው የድልድይ ግንባታ በባለሀብቱ በኩል ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ በአከባቢው ነዋሪዎች ስም አመስግነዋል።

የድልድዮቹ ግንባታ በክረምት ወቅት  ከአንድ ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ ለመሄድ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና ስቃይ እንደሚያስቀርላቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም