አገር በቀል እሴቶችን በማስጠናትና በመሰነድ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለማዋል እየተሰራ ነው

107

ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ)  አገር በቀል እሴቶችን በማስጠናትና በመሰነድ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲውሉ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ለኢዜአ እንደገለጹት የህዝብን ሰላም አስጠብቆ አብሮነቱን ለማጎልበት የሚያስችሉ ጠንካራ የሰላም እሴቶች በየአካባቢው ቢኖሩም በጥናት ዳብረው ለአገር ሰላም ግንባታ በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ አይስተዋልም።

ለአገር በቀል እሴቶች ትኩረት በመንፈግ የእኛ ያልሆነውን ልማድ መገለጫ አድርጎ መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ ትውልድ ለማነፅና ለሰላም ግንባታ የሚያግዙ አገር በቀል እሴቶችን ማጠናከር ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

አገር በቀል እሴቶች የሰላምና የህዳሴያችን መሰረት እንዲሆኑ ከምሁራን ጋር በትብብር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በዚህም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ አገር በቀል እሴቶችን ለሚፈለገው አላማ ለማዋል የማስጠናትና የመሰነድ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

 ትውልድን ለመቅረፅ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸው እነዚህ አካላት ስለ ሰላም፣  ስለሀገር ፍቅርና ስለአንድነት አበክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሰላም በአንድ ወገን ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ከትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት ጋር የሰላም ፎረም በማቋቋም በትውልድ ግንባታ ላይ በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በየአካባቢው የሚያጋጥመው የሰላም መደፍረስ በዘላቂነት መፍትሄ እንዲያገኝና በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እንዲረጋገጥ ለማድረግ ከክልሎች ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም