አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል--የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሰ መስተዳደሮች

11

ሰኔ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ)"አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ በሌሎች ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ የሚወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሳነ- መስተዳደሮችና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሽመልስ አብዲሳና ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን፤ ኮሚቴው በስብሰባው በወቅታዊ አገራዊ የጸጥታ ጉዳይ እና እየተወሰደ ባለው የሕግ ማስከበር እርምጃ ላይ ተወያይቷል።በዚህም አሸባሪ ቡድኖች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንጹሃን ላይ የፈጸሟቸውን ግድያዎች አውግዟል።

የሽብር ቡድኖቹ ይህን የቀቢጸ ተስፋ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት እየተወሰደባቸው ባለው ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ የደረሰባቸውን ኪሳራ ለመሸሸግ መሆኑን ኮሚቴው ገምግሟል።

የሕግ ማስከበር እርምጃው ከዚህ ቀደም የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ርዕሳነ- መስተዳደሮችና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት አቶ ሽመልስ አብዲሳና ዶክተር ይልቃል ከፋለ የሽብር ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆኑን ያረጋገጠ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፤ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የሽብር ቡድኑ ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዞ፤ በቡድኑ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሉ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ እጅግ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተመሳሳይ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎችን ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ህግ የማስከበር እርምጃ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም አሸባሪው ሸኔን ጨምሮ የህብረተሰቡን ሰላምና ድህንነት አደጋ ላይ ጥለው በነበሩ በርካታ ህገ-ወጥ ኃይሎች ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑ የጸጥታ ኃይሎች በሌሉባቸው አካባቢዎች በመሽሎክሎክ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዘ መሆኑን ጠቅሰው ኮሚቴው በቀጣይም ህግ የማስከበሩ እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በየትኛውም ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መሆኑን ያብራሩት ርእሳነ መስተዳደሮች፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን ጠብቀው የአገር ጠላት የሆኑ ኃይሎችን በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሸባሪው ሸኔ ከሰሞኑ የፈጸመው ጥቃትም ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማባላት ያለመ ሴራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት፡፡

ከዚህ አኳያ ህብረተሰቡ መንግስት እየወሰደ ላለው ህግ የማስከበር እርምጃ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ የሸኔ የሽብር ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመው ጥቃት የትኛውንም ብሔር የማይወክል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጠላት መሆኑን የሚያመላክት መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሽብር ቡድኑ ላይ ከሚወሰደው እርምጃ በተጓዳኝ ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን የማረጋጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም