የውሃ መስመር ቧንቧን በመስረቅ ወንጀል የተከሰሱ ግለሰቦች በፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

110

ሆሳዕና፤ሰኔ 15/2014 (ኢዜአ) ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ የውሃ መስመር ቧንቧን በመስረቅ ወንጀል የተከሰሱ ሶስት ግለሰቦች 7 ዓመት ከስምንት ወራት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን በሀድያ ዞን የአመካ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

በግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው በአመካ ወረዳ  አቢቾ ቀበሌ በተለምዶ ሙራሶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለህዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበረን የውሃ መስመር ቧንቧን ቆርጠው መስረቃቸውን በመረጋገጡ መሆኑን የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ዳኛ ጌታቸው ከበደ ገልጸዋል።

ከጥር 1 እስከ የካቲት 18/2014ዓ.ም፡ ባሉት የተለያዩ ቀናት ቧንቧውን ቆርጠው የውሃ አገልግሎት በማሰናከል ከ220 ሺህ ብር በላይ የሚገመት  ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አመላክተዋል።

በዚህም ቧንቧንም ሰርቀው  ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት በማስረጃ እንደተረጋገጠባቸው አስረድተዋል።

ፖሊስ ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተከታትሎ ግለሰቦቹን  መጋቢት 12/2014 ዓ.ም.በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ በአቃቢ ህግ በኩል ክስ እንደመሰረተባቸው ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ ከአቃቤ ህግ የቀረበለትን ክስ  የሰውና የሰነድ ማስረጃ መሰረት በማድረግ ጉዳዩን ሲመረምር መቆየቱን አስታውሰዋል።

አየለ አለሙ፣ ዳዊት ምትኩና አዱኛ በቀለ የተባሉት ግለሰቦቹ የህዝብ አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰው በመስረቅ ወንጀል የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል ባለመቻላቸው ጥፋተኝነታቸውን አረጋግጧል ብለዋል የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት።

ፍርድ ቤቱም ትናንት በዋለው ችሎት  እያንዳንዳቸው 7 ዓመት ከስምንት ወራት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን አስታውቀዋል።

ለማህበረሰብ ጥቅም ሀብት ፈስሶባቸው የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ ከባድ ወንጀል መሆኑን በመገንዘብ ማንኛውም ግለሰብ ከእንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሊቆጠብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም