በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተው በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን ማከናወን ያልቻሉ 912 ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዟል--የማዕድን ሚኒስቴር

18

ሰኔ 15/2014 ኢዜአ)  በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተው በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን ማከናወን ያልቻሉ 912 ኩባንያዎችን ፈቃድ መሰረዙን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የተቋሙን 11 ወራት አፈጻጸም አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የወጪ ንግድ ማዕድናትን በአይነትና በጥራት ማምረት በመቻሉ እየተገኘ ያለው ገቢ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት 11 ወራት ከወርቅ ምርት ብቻ 513 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም በውጪ ምንዛሪ ገቢ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው ሆኖ የተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ የተለያዩ የማእድን ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን ያላከናወኑ የተለያዩ ኩባንያዎች ላይ  ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም በማዕድን ፍለጋ ላይ የተሰማሩ 116 እንዲሁም ስድስት የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ፈቃድ ተሰርዟል ብለዋል።

በተጨማሪም በህገ-ወጥ ተግባር በተሰማሩ 850 ማዕድን ላኪዎች ፈቃድ እንዲሰረዝ መደረጉንም ጠቁመዋል።

መንግስት አዋጅ ከማሻሻል ጀምሮ ለዘርፉ ልማት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ገለጸው፤ ፈቃዳቸው የተሰረዘ ተቋማት ይህንን እድል መጠቀም ያልቻሉ  መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አሰራሮችን በመጣስ በህገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በዘርፉ የነበረው አሰራር ለሌብነት በር ከፋች እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ይህንን ችግር መቅረፍ የሚችል አሰራር ተዘርግቷል ነው ያሉት፡፡

መንግስት በዘርፉ ጥራት ያለው ምርት ማምረት የሚችሉ ኩባንያዎችን ለማሰማራት እየሰራ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም