የጤና ፕሮግራሞች የንቅናቄ መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን እየተካሄደ ነው

170

ጂንካ፤ሰኔ 14/2014(ኢዜአ) በ''ኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን'' እየተከናወኑ ያሉ የእናቶች፣የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት የጤና ልማት ፕሮግራሞችን ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ያለመ የንቅናቄ መድረክ በደቡብ ኦሞ ዞን ዲመካ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የንቅናቄ መድረኩ “የተቀናጀ የጋራ ጥረት ለፈጣንንና ተመጣጣኝ የእናቶች የጨቅላ ህጻናትና ህጻናት ጤና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ነው።

የመድረኩ  ዓላማ በፋውንዴሽኑ እየተከናወኑ ያሉ የእናቶች፣የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት የጤና ልማት ሥራዎች የአከባቢው ነዋሪዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ለማስቻል ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

በደቡብ ኦሞ ዞን በሐመርና በና ፀማይ ወረዳዎች በእናቶች፣ጨቅላ ህፃናትና የህፃናት የጤና ልማት እንክብካቤ ዙሪያ በፋውንዴሽኑ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

በህዝባዊ የንቅናቄ መድረኩ ላይ  የ''ኃይለማሪያምና የሮማን ፋውንዴሽን'' ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ፣ የፋውንዴሽኑ አጋር አካላት፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የደቡብ ኦሞ ዞን አመራሮች፣ የአከባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  እየተሳተፉ ነው።

በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ የተመሰረተው ፋውንዴሽኑ በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ ስርዓተ ምግብን፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ወጣቶች የስራ ፈጠራን እንዲሁም የአከባቢ ጥበቃና ኢኮ-ቱሪዝምን ዋና የትኩረት መስኮች አድርጎ በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የሚሰራ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት  ድርጅት መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም