በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በተፈጸመ ዝርፊያና ውድመት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት ደረሰ

ጎንደር፤ ሰኔ 13/2014 (ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ በተፈጸመ ዝርፊያና ውድመት ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ጉዳት መድረሱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት አስታወቀ፡፡


በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት እየደረሰ ያለውን ጉዳት መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ዛሬ ተካሂዷል፡፡


የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አበራ እንደገለጹት ጉዳቱ የደረሰው ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ ማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች ውስጥ በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ነው፡፡


የተደራጁ ቡድኖችና ግለሰቦች ባደረሱት ጉዳትም በከፍተኛ የሃይል መስመሮች፤ በትራንስፎርመሮችና በብረትና እንጨት ምሰሶዎች ላይ ዝርፊያና ውድመት መድረሱን አስታውቀዋል።


ጉዳቱን ተከትሎ በከተሞች በሚገኙ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የአገልግሎት መቋረጥ በማስከተል ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል።


ዘረፋና ውድመቱ የተቋሙን ገቢ ከማሳጣቱም በላይ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠሩንም ጠቁመዋል።


አጥፊዎች ላይ እየተወሰደ ባለው ህጋዊ እርምጃ ላይ የፍትህና የጸጥታ አካላት ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ የጎንደር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መንበሩ ማናዬ በበኩላቸው የኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ዝርፊያና ውድመት በሚፈጽሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ የሀገሪቱ ህግ ከ5 ዓመት እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተናግረዋል።


በዚህ አመት ብቻ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ዝርፊያና ውድመት ባደረሱ 14 ግለሰቦች ላይ ክስ በመመስረት ከ5 እስከ 11 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን ጠቁመዋል።


ሌሎች 14 ግለሰቦች ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው በኤሌትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ ዩኒቨርስቲው በሆስፒታሉና በማስተማር ሂደቱ ላይ መስተጓጎል እንደሚገጥመው ተናግረዋል፡፡


''በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ጉዳት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከባድ ነው'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግረዋል።


ከአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለፍትህና ለጸጥታ አካላት በተዘጋጀው የአንድ ቀን መድረክ ላይ ከጎንደር ከተማና ከሶስቱ ዞኖች የተውጣጡ ዳኞች አቃብያን ህጎችና የፖሊሲ አባላት መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም