የአዲስ አበባ ከተማ ሴት የምክር ቤት አባላት ኮከስ የተደራጀበት ዓላማ እንዲሳካ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ሴት የምክር ቤት አባላት ኮከስ የተደራጀበት ዓላማ እንዲሳካ አስተዳደሩ ድጋፍ ያደርጋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2014/ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ ሴት የምክር ቤት አባላት ኮከስ የተደራጀበት ዓላማ እንዲሳካ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሴት የምክር ቤት አባላት ኮከስ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ መደራጀት ኃይል በመሆኑ ለህዝባችን ድምጽና አለኝታ መሆን ይኖርብናል ብለዋል።
መደራጀት በራሱ ብቻውን ግብ ባለመሆኑ ውጤት ለማምጣትና በሴቶች ላይ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ኮከሱ አቅዶ በጋራ መስራት ይኖርበታል ነው ያሉት።
ኮከሱ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለመጪው ኮከስ መደላድል የሚሆኑ ተግባራትን ጭምር ማከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ኮከሱ የተደራጀለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለማስቻል ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር፤ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ መሻሻል እየታየበት ቢሆንም በአመራርና ውሳኔ ሰጪነት አሁንም በቂ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማስቀጠል የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናከሩ የኮከሱ አባላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በጉባኤው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የፌዴሬሽን ምክርቤት ምክትል አፈጉባኤ ዘሃራ ኡመድ እና ሌሎችም ሴት የምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ