የታዩትን ለውጦች በአዲሱ ዓመት ተቋማዊና ዘለቄታ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል - ዶክተር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
የታዩትን ለውጦች በአዲሱ ዓመት ተቋማዊና ዘለቄታ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል - ዶክተር አብይ
አዲስ አበባ ጳጉሜን 5/2010 በኢትዮጵያ የተጀመሩ ለውጦችን ተቋማዊና ዘለቄታዊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት "በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ባለው የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ባስተላለፉተ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ላይ ነው። ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ከባድ፣ አስቸጋሪና አደገኛ ጊዜ እንደሳለፈች አስታውሰው በዚህም ምክንያት አገሪቷ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊው፣ በማህበራዊና በተለያዩ መስኮች ቀውስ ውስጥ ገብታ እንደነበር አስታውሰዋል። ሰብአዊ ቀውስ አይሎ ኢትዮጵያ አንድነቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሸረሸረ የመጣበት ከባድ ጊዜም እንደነበር ተናግረዋል። ጥሩው ዜና ኢትዮጵያ አሁን ጉዞ እያደረገች ያለችው ወደ ተስፋ፣ ብርሃን፣ ይቅርታና ፍቅር እያመራች እንደሆነ ጠቅሰዋል። የ2010 ዓ.ም የመጨረሻ አምስት ወራት ወጋገን የታየባቸውና የአገርና የህዝብ ታሪክ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ መሸጋገሩ ገሃድ የሆነበት ወቅት እንደነበር አውስተዋል። ''በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው አዲሱ የለውጥ እርምጃዎች የፈነጠቃቸው የተስፋ ብርሃን ዘንጎች በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ መነቃቃትን ፈጥሯል'' ብለዋል። እርምጃዎቹ ለዓመታት ተኳርፈው የነበሩ እንዲታረቁ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የተለያዩ እንዲገናኙ ማድረጉን አስረድተዋል። የታዩትን ለውጦች በአዲሱ ዓመት ተቋማዊና ዘለቄታዊነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት። ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራና ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። አዲሱን ዓመት የምንቀበለው በስጋትና በተስፋ፣ በጨለማና በብርሃን፣ በጥላቻና ይቅርታና በቂምና በፍቅር መካከል ሆነን እንደሆነ መገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል። አዲስ ብርሃን ለመታየት የሚታገልበትን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ አዲስ ዓመት የተሞላ ንጋት ያላብሰው ዘንድ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በመደመር ለነገ ድምቀት በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።