በካምባ ወረዳ 600 ቤተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አነስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ሊገነባ ነው

88

ሰኔ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ 600 ቤተሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አነስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ሊገነባ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የግንባታ መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ግንባታው የሚካሄደው በካምባ ዙሪያ ወረዳ ድንጋሞ ቀበሌ ውስጥ በማይጽሌ ወንዝ ላይ ሲሆን የሃይል አቅርቦቱ ለወፍጮ፣ ለኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲሁም የተለያዩ የኤሌክትሪክ ሃይል ለሚፈልጉ አገልግሎቶች የሚውል እንደሆነ ተገልጿል።

“ክርስቲያን ኤይድ” ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወነው የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

የገጠር ማህበረሰቦችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበው ይህ ፕሮጀክት አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከክርስቲያን ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሚገነቡትም ተገልጿል፡፡

ግድቡ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ከ5 እስከ 10 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም