የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ ይገባል

82

ሰኔ 12/2014/ኢዜአ/ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ የሚገባ መሆኑን አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር ገለፀ።

የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር የተመሰረተበትን 15ኛ ዓመት አክብሯል።

የማኅበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዘሪሁን ሸለመ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ በባንኮች እምብዛም ተደራሽ ላልሆነው የማህበረሰብ ክፍል አገልግሎት ለመስጠት የቁጠባ ማህበራት ጉልህ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

አዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር ለዚህ ተጠቃሽና ተጨባጭ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቅሰው ሌሎችም ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን መስራት አለባቸው ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር በተለይም ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

በባንኮች የብድር አሰጣጥ ብዙም ተጠቃሚ ያልሆነውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ የብድርና ቁጠባ ማህበራት የላቀ ፋይዳ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከተበራከቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽና ተጠቃሚ ማድረግ ስለሚቻል ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማጠናከር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ዘርፉን ለማሳደግ የመንግስት ድጋፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የኅብረት ስራ ማኅበራትን በብዛት ከሶሻሊስት ሥርዓት ጋር የማያያዝ እሳቤ አለ" ያሉት አቶ ዘሪሁን አሜሪካና አውሮፓ በብዛት ሚጠቀሙበት አዋጭ ዘርፍ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ለዚህም 80 ዓመት የሞላውንና በ60 ሀገራት ቅርንጫፎች ያሉትን የኔዘርላንዱን "ራቦ" ባንክ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማኅበር በ1999 ዓ.ም 41 አባላትን በማሰባሰብ የተመሠረተ ሲሆን አሁን ላይ ከ200 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ በማሰራት ላይ ይገኛል።

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዓለም አቀፍ ኅብረት ሥራ ማኅበር አባልና የአፍሪካ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ኮንፌዴሬሽን ተባባሪ አባልም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም